የአፍሪካ ህብረት ስብሳባ ውጤታማና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ህብረተሰቡና የፀጥታ አካላት ለነበራቸው አስተዋፅኦ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ ምስጋና አቀረቡ

11ኛው የአፍሪካ ህብረት ልዩ ስብሰባ የህብረቱን ተልዕኮዎች በብቃት ሊያሳካ በሚችልበት መንገድ ለማደራጀት የሚያስችል ውሳኔ ማስተላለፉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየውን የህብረቱ 11ኛ ልዩ ስብሰባ መጠናቀቅ አስመለክቶ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው የአህጉሪቱ ዋና የለውጥ ሀይል የሆነው ወጣቱንና አፍሪካን ተሸክመው እዚህ ደረጃ ያደረሷትን የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያስችሉ ውሳኔዎች የተላለፉበት መሆኑን አንስተዋል።

በየክፍለ አህጉሩ ትብብርንና የጋራ ተጠቃሚነትን ማምጣት ስለሚቻልበት ሁኔታና ቀጣይ ጉዞም በስፋት እንደተመከረም ገልፀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በስብሰባው ምክንያት መንገዶች በአንዳንድ ቦታ ሲዘጉ እንደነበርና በዚህም የትራፊክ መጨነናቅ የተከሰተ ቢሆንም ህብረተሰቡ ያሳየው ትብብር እንደ ሁልጊዜው እንግዶቻችን ያስገረመ ነው ብለዋል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያደረገው እንግዳ ተቀባይ ድንቅ ህዝብ ከመሆኑም ባሻገር የተቀበለውን እንግዳ በቸር የመሸኘት ሀገራዊ ሀላፊነት በድርብ የተሰጡት ታላቅ ህዝብ በመሆኑ ነው ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ህዝብ ለለውጥ ሌት ተቀን እንደሚደክም ሁሉ ለውጡን ለማደናቀፍም ሌት ተቀን የሚደክሙ እኩያን የመኖራቸው ነገር ከማናቸውም ቢሆን የተሰወረ እንዳልሆነ  አንስተዋል።

ስብሰባው ውጤታማና ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሀገራዊ ሀላፊነታችሁን የተወጣችሁትን ሁሉ ከልብ አመሰግናላሁም ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው በተለያየ የስራ ዘርፍ የተሰማሩ አካላት፣ አጠቃላይ የሀገሪቱን ህዝቦች በተለይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን በራሴና በኢፌዴሪ መንግስት ስም በተለየ አክብሮትና ፍቅር ላመሰግናችሁ አወዳለሁ ብለዋል።