ግለሰቦች ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ሙስና በመፈጸማቸው ሃዘን እንደተሰማቸው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ

ሙያቸውንም ሆነ ሥልጣናቸው ያለአግባብ በመጠቀም  ግለሰቦች  አገሪቱን ለሃብት ብክነትና  ሙስና መዳረጋቸው ሓዘን እንደፈጠረባቸው በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ ሥራዎች  ላይ የተሰማሩ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች  ሰሞኑ ይፋ በሆነው የሙስና ወንጀል አሳዛኝ ድርጊት በጥልቅ ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአትክልት ንግድ ላይ የተሠማሩት ወጣቶቹ እንደሚገልጹት ዜጎች በአቋራጭ ከመበልጸግ ይልቅ  በላባቸው በሚያገኙት ገንዘብ እራሳቸውንና አገራቸውን ለማሳደግ ተገቢውን ሚና መጫወት  ይገባቸዋል ብለዋል ።

በአዲስ አበባ  በፅዳትና ውበት ስራ የተሰማሩት ወ/ሮ አበበች ወልደሀና እና አቶ ዳባሽ መንግስቴ በበኩላቸው ሌብነትን እንደሚጠየፉ በመግለጽ  የተለያዩ  ስልቶችን በመጠቀም  አገርን መበዝበዝ  ድህንትን  ለማስፋፋት በር የሚከፍት መሆኑን  ጠቁመዋል ፡፡

በሥራቸው ከሚያገኙት ገንዘብ ለአባይ ግድብ ግንባታ ገንዝብ ማዋጣታቸወን  በመግለጽ  ለግድቡ ግንባታ የተሰበሰበው ገንዘብ በሙስና መበላቱንና አለመበላቱን  መንግሥት በተገቢው  መንገድ ሊያጣራ  እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ወደፊት እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳይፈጸም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ ሌላውን ህብረተሰብ ማስተማር እንዳለበትም አክለዋል፡፡