ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ኢንቨስት አፍሪካ ከተባለ ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካን ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ኢንቨስት አፍሪካ ከተባለ ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካን ጋር ተወያዩ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ “ኢንቨስት አፍሪካ” የተባለውን ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካ ቡድንን በዛሬው እለት ነው በብሄራዊ ቤተ መንግስት ተቀብለው ያነጋገሩት።

በቆይታቸውም ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በሀገሪቱ እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ዙሪያ ለልኡካን ቡድኑ ገለፃ አድርገዋል።

በተጨማሪም ከልኡካኑ ለተነሳላቸው ጥያቄም ምላሽ መሥጠታቸው ነው የተነገረው።

በተያያዘ ዜና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍፁም አረጋ የኢንቨስት አፍሪካ ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካን ጋር በትናንትናው እለት መወያየታቸውን አስታውቀዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያ በመካሄድ ላይ የሚገኘው ፈጣን ለውጥ ለንግድና ኢንቨስትመንት እንዲሁም ለስራ ዕድል መስፋፋት አስተዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን ገለጻ አድርገውላቸዋል።

ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካኑ ላንሷቸው ጥያቄዎችም ምላሽ መስጠታቸውን አቶ ፍፁም አስታውቀዋል።

ኢንቨስት አፍሪካ የተባለው ዓለም አቀፍ የንግድ ልኡካን ቡድን በሀገሪቱ እየተፈጠረ የመጣውን የኢንቨስትመንት ዕድል ለማጥናት ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣው።

በልኡካን ቡድኑ ውስጥም 22 የእንግሊዝ እና የአሜሪካ የኩባንያዎች ኃላፊዎች ይገኙበታል።(ኤፍቢሲ)