ከአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ጋር በተያያዘ ሶስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገለጸ

ከአሶሳ ዩኒቨርስቲ ግጭት ጋር በተያያዘ ሦሰት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የአሶሳ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታወቋል ።    

በግጭቱ በቁጥጥር ሥር የዋለውን ግለሰብ “ታምሚያለሁ” በሚል ወደ መኖሪያ ቤቱ እንዲሄድ በመፍቀድ በግለሰቡና በፀጥታ ኃይሎች መካከል ውጥረት በመፍጠር የተጠረጠሩ ሶስት የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር  የዋሉት ።

የአሶሳ ከተማ ፖሊስ አዛዥ ኮማደር አኑር ሙስጠፋ እንዳስታወቁት በከተማው የወረዳ ሁለት መደበኛ ፖሊስ አባላት ባልደረቦች  የሆኑ ሶስት ግለሰቦች ማምሻውን ትጥቃቸውን ፈትተው በቁጥጥር ሥር ውለዋል፡፡

የፖሊስ አባላቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉት በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ተጠርጥሮ በቁጥጥር ሥር የዋለው ግለሰብ ላቀረበው የ”ታምሚያለሁ” ጥያቄ ጉዳዩ ከሚመለከተው የወረዳው አካል ትዕዛዝ ሳያገኙ በራሳቸው ፈቃድ ግለሰቡን ወደ መኖሪያ ቤቱ በመውሰዳቸው ነው፡፡

የጸጥታ ሃይሎቹ ተጠርጣሪውን ወደ ህክምና ተቋም መውሰድ ሲገባቸው ወደ መኖሪያ ቤቱ መውሰድ እንዳልነበረባቸው ኮማንደር አኑር አስረድተዋል፡፡

ግለሰቡም ወደ መኖሪያ ቤቱ በተወሰደበት ወቅት ክላሽንኮብ በማውጣት በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጥቃት ለማድረስ ሙከራ ማድረጉን አስረድተዋል፡፡

ይህንኑ ተከትሎ በከተማው በተወሰኑ ቦታዎች አለመረጋጋት ታይቶ እንደነበረ ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ግን የከተማው ሁኔታ በጸጥታ ሃይሎች እና በህብረተሰቡ ትብብር ወደ ነበረበት እንደተመለሰ አስታውቀዋል፡፡ (ኢዜአ)