በአገሪቱ ሰላም ከማስከበር አንጻር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው- ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል

በአገሪቱ ሰላም ከማስከበር አንጻር የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ትልቅ ድርሻ አላቸው ሲሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል ገልጸዋል፡፡

በወቅታዊ የኢትዮጵያ የሰላም ጉዳይ ላይ ኪነ-ጥበብ የራሱን አስተዋፅኦ ሊያደርግ ይገባል በሚል ሃሳብ ላይ ከባለሙያዎች ጋር ምክክር ለማድረግ ነው መድረኩ የተዘጋጀው፡፡

የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ብልሹ አሠራሮችን በማጋለጥና የሰላምን አስፈላጊነት በመስበክ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚገባቸው ወይዘሮ ሙፈሪያት አስረድተዋል፡፡

የኪነ-ጥበብ ባለሙያው የማህበረሰብ አስተሳሰብ ለማምጣት ያለባቸውን ኃላፊነት ለመወጣት ግንባር ቀደም መሆን ይገባቸዋልም ተብሏል፡፡

ጋዜጠኛና ደራሲ አበረ አዳሙ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቲያትር ትምህርት ቤት ኃላፊና አቶ ተስፋዬ እሸቱ ኪነ-ጥበብ ለሰላም ባለው ጉዳይ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበዋል፡፡

ስለ ሀገር ፍቅር የሚያቀነቅኑ እና ወኔ የሚቀሰቅሱ አንድነትን የሚሰብኩ ሙዚቃዎች፣ ቲያትሮች እንዲሁም መፅሐፍት ቀደም ባለው ጊዜ ነበሩ አሁን ግን እየቀዘቀዙ መጥተዋል ሲሉ ባለሙያዎቹ ተችተዋል፡፡

ይህ እንዳይቀጥል መሥራት አለበት ሲሉም ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡