ኦዴፓ እና ኦዴግ አብረው ለመስራት የውህደት ስምምነት ተፈራረሙ

የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኦዴግ) አብረው መስራት የሚያስችላቸውን የውህደት ስምምነት በዛሬው ዕለት ተፈራርመዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች የኦሮሞ ህዝብ ከብዙ ፓርቲ ይልቅ አንድ እንዲሆኑና በምርጫ ድምጻቸውን ለመሥጠት እንዲያመች በጠየቁት መሠረት መዋህዳቸውን የኦዴፓ የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ለሚዲያ በሠጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ፓርቲዎቹ ከፉክክር ይልቅ የመተማመንና አብሮ በመሥራት  የህዝብ ጥያቄ ለመመለስ በሚል ውህደት መፍጠራቸውን ነው አቶ አዲሱ የገለጹት፡፡

አቶ አዲሱ አያይዘውም ኦዴፓ ከኦዴግ ጋር የህገ ደንብ፣ የስትራቴጂ፣ የፕሮግራም እንዲሁም የርዕዮተ ዓለም ልዩነት እንደማይኖራቸውም ተናግረዋል፡፡

ሁለቱ ፓርቲዎች የተዋህዱት ተጠናክረው የዴሞክራሲ ግዴታቸውን እንዲወጡ ለማስቻል ነውም ብለዋል፡፡

በቀጣይም ከሁለቱ ፓርቲዎች የተውጣጡ አባላት ያሉበት የቴክኒካል ኮሚቴ ተቋቁሞ የሀብት አጠቃቀም፣ የሰንደቅ ዓላማ አጠቃቀም፣ በአባላት ህገ-ደንብ ዙሪያ እንዲሁም ሌሎች ጉዳዮች ላይ አብሮ እንደሚሠሩ ገልጸዋል፡፡

በጋራ ለመስራት የሚደረገው የውህደት ሂደት እንደሚቀጥል ያነሱት አቶ አዲሱ አሁን ላይም ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር የተጀመሩ ውይይቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።