የኦብነግ ከፍተኛ አመራሮች ቅዳሜ ኢትዮጵያ ይገባሉ

የኦጋዴን ብሄራዊ ነጻ አውጭ ግንባር (ኦብነግ) ከፍተኛ አመራሮች በመጪው  ቅዳሜ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ  ተገለጸ ፡፡

ቅዳሜ የሚገቡት ሊቀመንበሩ መሐመድ ኦማርን ጨምሮ ከ20 በላይ ከፍተኛ አመራሮች መሆናቸውን የግንባሩ ቃል አቀባይ በዛሬው ዕለት በሠጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

ቃልአቀባዩ እንደገለጹት ቅዳሜ ዕለት አዲስ አበባ ለሚገቡት አመራሮች ወጣቶች አቀባበል እንዲያደርጉላቸው ጠይቀዋል፡፡

ቃልአቀባዩ በሰጡት መግለጫ የክልሉን ህዝቦች ተጠቃሚ በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ አትኩረው እንደሚንቀሳቀሱ ገልጸዋል፡፡

ከሳምንት በፊት የኦብነግ ሰራዊት ትጥቅ በመፍታት ከአስመራ ወደ ጅግጅጋ መግባቱ ይታወሳል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የተመራ ልዑክ ወደ ኤርትራ በማምራት ከቡድኑ ጋር ባደረገው ድርድር ስምምነት ላይ መድረሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

በዚህም ለረጅም አመታት የትጥቅ ትግልን አማራጭ አድርጎ ሲንቀሳቀስ የቆየው ግንባሩ፥ ወደ ሀገር ቤት ተመልሶ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ስምምነት ላይ መድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ገልፀው ነበር።

የኦጋዴን ብሄራዊ ነፃ አውጭ ግንባር ከስምምነቱ ቀደም ብሎ ልዑኩን ወደ ሀገር መላኩም ይታወሳል።

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያቀረቡትን የሰላም ጥሪ ተከትሎ መቀመጫቸውን በውጭ ሀገር ያደረጉ ኃይሎች የትጥቅ ትግል በማቆም ወደ ሃገር ቤት ገብተዋል።(ኤፍቢሲ)