በምስራቅ ወለጋ ዞንና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወት ማለፉ ተገለጸ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን እና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አዋሳኝ አካባቢ በተፈጠረ ግጭት የሰው ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የኦሮሚያ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በግጭቱ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስን ጨምሮ የበርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ህይወት ማለፉን ገልጸዋል፡፡

እንዲሁም ለጊዜው ግምቱ ያልታወቀ በርካታ ንብረት መውደሙን የተናገሩት አቶ ዴሬሳ ችግሩ ያጋጠመው ባሳለፍነው ማክሰኞ ህዳር 18፤ 2011 ዓ.ም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ አርቁምቤ በሚባል አካባቢ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በግጭቱም በአካባቢው ነዋሪዎች እና በኦሮሚያ ፖሊስ አባላት ላይ አሰቃቂ ወንጀል ተፈጽሟል ያሉት አቶ ዴሬሳ፥ በግጭቱ ህይወታቸው ያለፈ እና የተጎዱ ሰዎች ቁጥር በቅርቡ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል።

በግጭቱ ህይወታቸው ያለፈ ሰዎች አስክሬን በትናንትናው እለት ነቀምቴ ከተማ ሲገባ ህዝቡ ሰልፍ በመውጣት ስሜታዊ በመሆኑ የአንድ ሰው ህይወት ማለፉንም ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው አቶ ዴሬሳ ተረፈ፥ በምዕራብ ኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ዋነኛ ምክንያት የክልሉን እና የሀገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ እንዲሁም አሁን በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አካላት ናቸው ብለዋል።

የእነዚህ አካላት እቅድም እንደ ኦሮሚያ ክልል እና እንደ ሀገር እየመጣ ያለውን ለውጥ ማደናቀፍ በመሆኑ ህዝቡ ከስሜታዊነት በመውጣት መንግስት ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ የሚወስደውን እርምጃ እንዲደግፍ ጥሪ አቅርበዋል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)