ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ከተለያዩ የአረብ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያዩ

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ መቀመጫቸውን በአዲስ አበባ ካደረጉ የተለያዩ የአረብ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸውም በኢትዮጵያና በአረብ ሀገራት መካከል ሰፊ የሆነ የባህልና የረጅም ጊዜ ግንኙነት መኖሩን የጠቀሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፥ ይህ ግንኙነት በተጠናከረና ውጤታማ በሆነ መልኩ እንዲቀጥል የኢትዮጵያ ጽኑ ፍላጎት ነው ብለዋል።

የአረብ ሀገራት አምባሳደሮች በበኩላቸው፥ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸው ታሪካዊ ትስስርና አጋርነት የጋራ ተጠቃሚነትን በሚያጎለብት መልኩ እንዲጓዝ ሃገሮቻቸው ጠንክረው እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

በተያያዘ ዜና የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሃላፊ ካሮሊን ቱርክ ጋር ተየዋይተዋል።

በውይይታቸውም በአለም ባንክ እና በኢትዮጵያ መንግስት መካከል ባለው አጋርነት የተገኙ ውጤቶችንና ቀጣይ ትብብሮችን ላይ ትኩረት አድርገዋል።

የአለም ባንክ በኢትዮጵያ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ ጉልህ ድርሻ እንዳለው ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ፤ በተለይም በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ የተያያዘችውን የለውጥ ጉዞ በሚደግፍ መልኩ ትብብሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በአለም ባንክ የኢትዮጵያ፤ ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ሃላፊ ካሮሊን ቱርክ በበኩላቸው፥ ሀገሪቱ የተያያዘችውን ሁለንተናዊ የለውጥ እርምጃዎች የሚደገፉ እና ባንኩም በሁሉም ረገድ ድጋፉን የሚሰጥባቸው ናቸው ማለታቸውን የፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት አስታውቋል።