የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊ ከኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዶ/ር ወርቅነህ ጋር ተወያዩ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር ቲቦር ናጊን በፅህፈት ቤታቸው በመቀበል  ውይይት አደረጉ ።

የአፍሪካ ቀንድ ለአፍሪካ ተስፋ መሆኑን የጠቆሙት ረዳት ሚኒስትሩ፥ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እና መረጋጋት እንዲረጋገጥ  እየተጫወተች ያለውን የመሪነት ሚና ምስጋና አቅርበዋል።

ዶክተር ወርቅነህ በውይይቱ እንደገለጹት ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ጋር በመሆን በልማት እና ፀጥታ ጉዳዮች ላይ የተጠናከረ ሥራ የምታከናውን ሲሆን፥ በቀጠናው ሰላም እንዲሰፍን አሜሪካ ለምታደርገው ድጋፍ አመስግነዋል፡፡   

ኢትዮጵያና አሜሪካም በኢንቨስትመንት እና በንግዱ ዘርፎች ያላቸውን ግንኙነትንም ይበልጥ ለማሳደግ ፍላጎት እንዳለ የገለፁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፥ በጋራ በመሥራት የሁለቱ አገራት ህዝቦችን ተጠቃሚነት ማሳደግ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡ 

አሜሪካ በኢትዮጵያ የትምህርት፣ ጤና እና የሃይል ልማት እንዲጠናከር ትብብርና ድጋፍ  እያደረገች መሆኑን ዶክተር ወርቅነህ ተናግረዋል።

ቲቦር ናጊ በበኩላቸው ከውይይቱ በኋላ እንደገለጹት  ፥ ኢትዮጵያ ለአካባቢው ፖለቲካዊ  ሁኔታ መለወጥ ምክንያት መሆኗንና ለአፍሪካም እንደ አብነት የምትጠቀስ ሀገር ናት ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያና ከኤርትራ የፈጠሩትን ያለመግባባት ወደ ትብብር በመቀየሩ የአሜሪካ መንግስት ከፍተኛ አድናቆት ያለው መሆኑን ገልጸዋል፡፡       

ኢትዮጵያ በቅርቡ በአፍሪካ ቀንድ ዘላቂ ሰላም እና መረጋጋት እያደረገች የሚገኘውን አስተዋጽኦ ተጠናክሮ ለማስቀጠል የአሜሪካ ድጋፍ እንደማይለያት ቲቦር ናጊ ተናግረዋል፡፡