ብሔራዊ የጸጥታ ም/ቤት የፌደራል ጸጥታ አካላት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች እንዲሰማሩ ወሰነ

ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት የፌደራል ጸጥታ አካላት በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተሰማርተዉ የህግ የበላይነትን አንዲያስከብሩ ወሰነ፡፡

የጸጥታ አካላቱ የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ወደ ቤት ንብረታቸዉ በመመለስ መልሶ እንዲያቋቁሙና ሰላም እንዲያሰፍኑ በምክር ቤቱ ኃላፊነት ተሰጥቷቸዋል ።

ችግሩ ከሁለቱ ክልሎች አቅም በላይ መሆኑን በህገ መንግስቱ መሰረት የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ችግሩን እንዲያረጋጋ በጠየቁት መሰረት መሆኑን የብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ያወጣው መግለጫ ያስረዳል፡፡

 

የምክር ቤቱ ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ አስተማማኝ ሰላምን በማስፈን የሕዝብን ደኅንነት ማስከበር የመንግሥት ቀዳሚ ተግባር ነው!

ሕገ-ወጦችና ወደ ሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል!!

በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጵያ በፖለቲካ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የለውጥ ሂደት ላይ ትገኛለች። ለውጡ በሕዝባችን ትግልና ግፊት የመጣና አገራችንን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚያሻግር፣ ለአገራችን ዘላቂ ብልጽግና መሠረት የሚጥልና የዜጎችን መሠረታዊ ሰብዓዊ መብቶች የተከበሩበት የመንግሥት አስተዳደር ለመዘርጋት የሚያስችል ነው።

ለውጡን ተቋማዊና ዘላቂ ለማድረግ መንግሥት የተቋማት፣ የሕግ እና የፖሊሲ ማሻሻያ ሥራዎችን እየሰራ መሆኑ ይታወቃል። የሕዝብ አመኔታና ቅቡልነት ያላቸው ተቋማትን ለመገንባት ተዓማኒነትና ተገቢ ልምድ ያላቸውን ሰዎች ከመሾም ጀምሮ ዘርፈ-ብዙ ሥራዎች ተጀምረዋል።

በዚህ ሕዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ጥቅማቸው የተነካ የተለያዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕዝባዊውን የለውጥ ሒደት ለማደናቀፍ፣ በሕዝቦች መካከል ለዘመናት የኖረው አብሮ የመኖር፣ የመቻቻልና የመረዳዳት ባሕል ተሸርሽሮ በምትኩ ቂምና ቁርሾ እንዲኖር፣ በበሂደትም ግጭት ተስፋፍቶ ሞት ፣ መፈናቀል እና ሌሎች ሰብዓዊ ቀዉሶችን በማስፋፋት ግርግር ለሌባ ያመቻል እንደተባለዉ ለዉጡን በመቀልበስ ለሌብነት፣ለዝርፊያ አና ሰብዓዊ መብቶችን እንዳሻቸዉ እየጣሱ ያለተጠያቂነት መኖር የሚያስችላቸዉን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

መንግሥት ህግን በማስከበር በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በአገር ሀብት ዝርፊያ በመፈጸም የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ መዉሰድ የጀመረዉን እርምጃ አቅጣጫ ለማሳት እና ለመቀልበስ ሲረባረቡ ይስተዋላል።

እነዚህ ኃይሎች የተጀመረውን ለውጥ በማደናቀፍ የግል ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ የብዙ ንጹህ ዜጎችን ሰላምና አንዲሁም የሀገራቸንን ደኅንነት አደጋ ላይ ለመጣል በመንቀሳቀስ ይገኛሉ።

በዚህም ምክንያት ከህግ ተጠያቂነት ለማምለጥ ሲሉ በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች አቅደዉ ግጭቶችን በመቀስቀስ በሰዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንዲደርስ ምክንያት ሆነዋል፣ ብዙዎችም ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ይህንን ችግር በመቅረፍና ለግጭቶቹ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦችን ወደ ሕግ ለማምጣት በችግርና በእንግልት ላይ ላሉ ዜጎችም ድጋፍ ለማድረግ መንግስት ህዝቡን በማስተባበር ሰፊ ርብርብ ሲያደርጉ እንደቆዩ ይታወቃል።

ሆኖም ግን እነዚህ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች እየታዩ በመሆናቸው የተጠናከረ ምላሽን የሚጠይቁ ሆነዉ ተገኝተዋል፡፡

የመንግሥት ቀዳሚ ግዴታ የሕዝባችንን ደኅንነት መጠበቅና የሕግ የበላይነትን ማክበርና ማስከበር ነው። በመሆኑም ኢፌዴሪ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት በቅርቡ በምዕራብ ኢትዮጵያ በኦሮሚያና በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር እና ሰብዓዊ ቀዉስ አስመልክቶ ዛሬ ሕዳር 22 ቀን 2011 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ በጥልቀት መክሯል።

ምክር ቤቱ በአካባቢው የነበረውን ኢትዮጵያ: አዲሲቷ የተስፋ አድማስ Ethiopia: A New Horizon of Hope የጸጥታ ችግር ለመፍታት ጉዳቱን በጥልቀት በመገምገም ከክልሎቹ መንግሥታት ጋር ባደረገዉ ዉይይት የአካባቢዉን ሰላም የማስከበር፣ የዜጎቸን ህይወት የመታደግ እና በአከባቢዉ የህግ የበላይነትን በማስከበር አስተማማኝ ሰላም አና ጸጥታን የማስፈን ጉዳይ ከሁለቱ ክልሎች አቅም በላይ መሆኑን እና የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በህገ መንግስቱ መሰረት ጣልቃ ገብተዉ ችግሩን እንዲያረጋጉ ክልሎቹ በጠየቁት መሰረት የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት በአካባቢው ተሰማርተዉ የህግ የበላይነትን እንዲያስከብሩ፤የተፈናቀሉ ዜጎቻችን ወደ ቤትና ንብረታቸዉ መልሶ በማቋቋምና ሰላም አንዲያሰፍኑ ወስኗል።

በመሆኑም በአካባቢዉ የፌዴራል መንግስት የጸጥታ አካላት አካባቢውን የማረጋጋት ሥራ ይሠራሉ፤ በአካባቢው ያለውን ማንኛውንም ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በመቆጣጠር ተጠርጣሪዎችን ወደ ሕግ የሚያቀርቡ ይሆናል።

መንግሥት የሕግ የበላይነትንና የሕዝባችንን ደኅንነት ለማረጋገጥ የጀመረዉን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ኃላፊነቱን ይወጣል። እንዲሁም ይሄ እርምጃ በተለያዩ ክልሎች ዉስጥ በተመሳሳይ መልኩ ተጠናክሮ ይቀጥላል። የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የዲሞክራሲና የልማት ሕልም ዕውን የሚሆነው ሕግና ሥርዓት ሲኖር ነው።

ሕገ-ወጥነትና ሥርዓተ-አልበኝነት ባለበት አገር ውስጥ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታም ሆነ ዕድገት ከቶ ሊታሰብ አይቻልም።

በመሆኑም የፌደራልና የክልል መንግሥታት አካላት የሕዝብና የአገር ጸጥታና ደህንነት ለማረጋገጥ በሚደረገዉ እንቅስቃሴ ምዕላተ ህዝቡን ከመንግስት ጎን በመቆም ለዉጡን እዉን ለማድረግ የማይተካ ሚናዉን ሲወጣ እንደቆየ አጠናክሮ እንዲቀጥል የኢፌድሪ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤት ጥሪዉን ያስተላልፋል፡፡