ኦብኮ ከኦዲፒ ጋር ለመዋሃድ የሚያስችለውን ውሳኔ አሳለፈ

የኦሮሞ ብሔራዊ ኮንግረስ (ኦብኮ) ከኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) ጋር ለመዋሃድ የሚያስችለውን ውሳኔ አሳለፈ፡፡

የኦብኮ ሊቀመንበር አቶ ቶለሳ ተስፋዬ እና አመራሮቹ ውሳኔውን በማስመልከት መግለጫ ሠጥተዋል፡፡

ፓርቲው በመግለጫው ከኦዴፓ ጋር የፕሮግራምና የሐሳብ ልዩነት እንደሌለው ገልጾ ህዳር 14 ባካሄደው የድርጅቱ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ከኦዴፓ ጋር ለውህደት የሚያበቃ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል፡፡

በዚህም ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከኦዴፓ ጋር የውህደት ስምምነት ለማድረግ ጥሪ ማቅረቡን ገልጿል፡፡  

አብኮ ህገመንግስቱ ከጸደቀ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም በ1988 ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ህጋዊ ፍቃድ አግኝቶ የፖለቲካ ጎራውን መቀላቀሉን በመግለጫው ጠቅሷል፡፡

በ1997 ዓ.ም በተከናወነው ምርጫም በክልል ምክር ቤት 105 መቀመጫና በፌደራል ምክርቤት 38 መቀመጫዎችን አግኝቶ እንደነበር ፓርቲው አስታውሷል፡፡