የየመን ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ መሥጠት እንደሚገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የየመን ተፋላሚ ኃይሎች ለሰላማዊ መፍትሄ ቅድሚያ እንዲሠጡ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በየመን እየተፋለሙ ላሉ ሁሉም አካላት ባስተላለፉት መልዕክት፥ ጦርነት ጥፋትን፣ ውድመትን እና መለያየትን የሚያመጣ እንደመሆኑ ሁሉም ተሸናፊ ነው ብለዋል  የጠቅላይ ሚንስትር ጽህፍት ቤት ባወጣው መግለጫ ።

እንዲህ አይነት ነገር እንዴት በአንድ መሬት ላይ በሚኖር የአንድ ሀገር ህዝብ ላይ ይከሰታል ሲሉም ጠይቀዋል።

“ጦርነት መሰረታችሁን፣ ግንኙነታችሁን፣ መልካምነታችሁን ያጠፋል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ ከጦርነት የሚገኘውም ከጥፋት ውጪ ምንም ነገር እንደሌለ አስታውቀዋል።

“ሁሉንም የሀገሪቱን ክፍል በምታወድሙበት ጊዜ የመን ለምን እየተዋጋች ነው የሚለውን ለምን አታሰቡም፤ ከጦርነት እና ግጭት ቋንቋ ይልቅ በንግግር የማመን ቋንቋን ለምን አታስተምሩም” ብለውም ጠይቀዋል።

“ለምን በጠረጴዛ ዙሪያ ቁጭ ብላችሁ መልካሙ ነገር ምንድን ነው በሚለው ላይ አትወያዩም?” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በዚህ መልኩም እንደ አንድ ቤት ህዝብ ያለምንም ደም መፋሰስ እና ጦርነት በነገሮች ላይ አለመግባባት እና መግባባት ትችላላችሁ ብለዋል።

“በአሁኑ ወቅት ሀገራችሁ ላለችበት እያንዳንዱ ነገር ሁላችሁም ኃላፊነት የምትወስዱ እና ተጠያቂዎች ናችሁ” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ “ሀገራችሁ ሰላማዊ እንድትሆን እጅ ለእጅ ለመጨባበጥ እና በሙሉ ልብ ለመቀራረብ ቀዳሚ መሆን አለባችሁ” ብለዋል።

ከግል ፍላጎታቸው ይልቅ በአንድነት በመሆን ለሀገሪቱ የሚበጁ መልካም ነገሮችን በማሰብ ለሀገራቸው በጋራ እንዲሠሩም ጥሪ አቅርበዋል።

በጦርነት የተጎዳውን የሀገሪቱን ህዝብ ፍላጎት በማስቀደም በሚያስማማቸው ጉዳዮች ላይ ተባብረው በጋራ ሊሰሩ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በመልዕክታቸው፥ ሁሉም ተፋላሚ ኃይሎች ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እንዲፈቱም ጥሪ አቅርበዋል።(ምንጭ : የጠቅላይ ሚኒስትር ፀህፈት ቤት )