መንግሥት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ከግብ ለማድረስ እንደሚሠራ ተገለጸ

መንግስት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የያዘውን ቁርጠኛ አቋም ከግብ ለማድረስ እንደሚሰራ የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ አስታወቀ፡፡

የፌደራል ጠቅላይ አቃቢ ህግ በዛሬው እለት ለዋልታ በላከው መግለጫ ሀገሪቱ በለውጥ ጎዳና ላይ በመሆኗ የተጀመረውን ለውጥ  ከግብ ለማድረስና የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ ብሎም ለዜጎች ምቹ አገር ለመገንባት ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች ብሏል፡፡

በዚህ ሂደት ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሕዝቡ በፍትህ ሥርዓቱ የሚያነሳቸውን ቅሬታዎችን ለመፈታት የማያቋርጥ የአሰራር ስርዓትና የአደረጃጀት ለውጥ በማድረግ መልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ጥረት  በመደረግ ላይ ይገኛል ።

በአገሪቱ የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና  የለውጥ ጉዞ ምን ጊዜም ቢሆን ወደ ማይቀለበሰበት ደረጃ ለማድረስ እና የፍትህ ሥርዓቱን አሠራር ውጤታማ፤ ቀልጣፋና ተደራሽ በማድረግ የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ከምንጊዜውም በላይ በትጋት በመሥራት ላይ ነው ብሏል፡፡

ለአብነት በቅርቡ በሰብአዊ መብት ጥሰትና በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በህግ ጥላ ሥር የዋሉት አካላት የለውጡ ጅማሮ ተደርገው ሊወሰዱ ይችላሉ ብሏል፡፡

የህግ የበላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ተፈጥራ የማየት፣ እኩልነት የተረጋገጠባት ሀገር መገንባትና በፍትህ ሥርዓቱ ከህግ ውጭ የሆኑ ተግባራት ሲፈጸሙ ፈጻሚው አካል በብሄሩ፣ በሃይማኖቱ፣ በማንነቱ ሳይሆን በሠራው ወንጀል ልክ ሕግን ማዕከል ያደረገ  ተጠያቂነት በማስፈኑ ረገድ ትልቅ ስራ እየተሰራ ነው ተብሏል፡፡

በቀጣይም በተደራጁ የኢኮኖሚ አሻጥር፣ ሙስናና ሌብነት እንዲሁም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉ ሕገ-ወጦችን ወደ ሕግ የማቅረቡ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አንስቷል፡፡

አገሪቱ ላለችበት ለውጥ ወሳኝነቱ የጎላ በመሆኑ መንግስት ይህንን አካሄድ ተከትሎ ከሕግ ውጭ የሆኑ አካላትን ለሚፈጽሙት ተግባር የማይታገስና ለድርድር የማይቀርብ መሆኑን ያነሳው መግለጫው ተጠያቂ እንዲሆኑም ሌት ተቀን ይሰራል ብሏል፡፡