የፌደራል ፖሊስ በኦሮሚያና ቤኒሻንጉል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር መፍታት የሚያስችል ሥራ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ

የፌደራል ፖሊስ በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል አዋሳኝ አካባቢዎች የተፈጠረውን ችግር መፍታት የሚያስችል ሥራ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መሥራት መጀመሩን አስታወቀ፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌዴራል ፖሊስ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ጃላን አብዲ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በሚያስችል መልኩ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁን አስታውቀዋል፡፡

በአካባቢው ባለፉት ሳምንታት በተፈጸመ ጥቃት የሰው ህይወት መጥፋቱንና በንብረትም ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱን ገልጸዋል፡፡

የተፈጸመው ወንጀል ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በድርጊቱ የተሳተፉትን አካላት ለህግ የማቅረብ ስራ መጀመሩንም አክለዋል፡፡

በተጨማሪም በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በሚነሱ ግጭቶች በዜጎች ላይ ከፍተኛ ችግር እየደረሰና ሰላም እየደፈረሰ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሀገር ዓቀፍ ግብረኃይል ተቋቁሞ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል፡፡

በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች እየተፈጠሩ ካሉ ችግሮች ጀርባ ለውጡን ያልተቀበሉና በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አካላት እጅ እንዳለ ፖሊስ ማረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

ወንጀል የፈጸመ ማንኛውም ሰው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር በህግ ቁጥጥር ስር መዋሉ አይቀርም ያለው አቶ ጃላን የወንጀሉ ተሣታፊ የሆኑ አካላት ከዚህ ድርጊት መታቀብ እንዳለበትና ህብረተሰቡም ፖሊስ ለሚያደርገው ስራ ድጋፍ እንዲሰጥ ጥሪ አቅርቧል።