የ13ኛውን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዓልን ለማክበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ

የ13ኛውን ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዝቦች በዓልን ለማክበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የከተማ አስተዳደሩ አስታወቀ፡፡

በዓሉን አስመልክቶ መግለጫ የሰጡት የከንቲባው ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬቴሪ ወሪት ፌቨን ተሾመ እንደገለጹት 1500 የባህል ቡድኖችን ጨምሮ 2 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን በዓሉን ለመታደም ወደ መዲናዋ ይገባሉ፡፡

በበዓሉ ወቅት ብሄራዊ ሃብት የሆነውን ቡናን ለማስተዋወቅ 10ሺህ ሰዎች የሚታደሙበት የቡና ማፍላት ሥነ-ሥርዓት እንደሚከናወን እና ዝግጅቱን በዓለም  የድንቃድንቅ መዝገብ (በጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ)  ላይ ለማስመዝገብ ጥረት እንደሚደረግም በመግለጫው ተናግረዋል፡፡

ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ሆቴሎች መዘጋጀታቸውን የገለጹት ወይዘሪት ፌቨን የከተማው ወጣቶችም አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቀው እንግዶቻቸውን እየተቀበሉ መሆኑን ገልጸዋል።

በዓሉን በሰላማዊ መንገድ እንዲከበር እና እንግዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ እንዲመለሱ የከተማው የፀጥታ ኃይል አስፈላጊውን መሰናዶ ማጠናቀቁንም አንስተዋል፡፡

ዋናው በዓል በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚከበር ሲሆን በዕለቱ ከንቲባውን ጨምሮ 30 ሺ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች ይታደማሉ ተብሏል  ፡፡ (ምንጭ፡-የከተማ ከንቲባ ጽህፈት ቤት)