የአገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት ሊወጡ እንደሚገባ ሴት የሰላም አምባሳደሮች ጠየቁ

የአካባቢያቸውን ብሎም የሀገራቸውን ሰላም ለማረጋገጥ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ሀላፊነት መወጣት እንደሚገባቸው  ሴት የሰላም አምባሳደሮች ጠየቁ፡፡

ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ በድሬዳዋ ከተማ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በሰላም ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡

ከዘጠኙም ክልሎችና ሁለት ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ 21 የሰላም አምባሳደር እናቶች ባለፉት ሁለት ቀናት በድሬዳዋ ቆይታ አድርገዋል ።

 የሰላም አምባሳደሮች በድሬዳዋ ቆይታቸውም ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ኃይማኖት አባቶች፣ ወጣቶች፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችና ከፍተኛ የመንግስት አመራሮች ጋር በሰላም ዙሪያ ምክክር አድርገዋል፡፡ 

ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ በቆይታቸው ግጭትና መፈናቀል ሲከሰት ዋንኛ ተጎጂዎቹ ሴቶች ከመሆናቸው ባለፈ በሀገር ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖም ከፍተኛ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡  

በቀጣይም ሀገራችን ሰላም እንድትሆን በመሥራት ግጭቶች እንዳይከሰቱ የሰላም አምባሳደሮቹ የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ቃል ገብተው የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችም ለሰላም በጋራ መስራት እንደሚገባቸው ተናግረዋል፡፡    

የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማን እንደገለጹት ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ የሰነቁት አላማ እንደ ሀገር ብሎም ለቀጠናው ሰላም መረጋገጥ በእጅጉ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረው በጥቃቅን ችግሮች የነበሩንን እሴቶች መሸርሸር እንደማይገባና በቀጣይ ለሚደረጉ የተለያዩ የልማት ስራዎች ሁሉ ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ ድጋፍ አጋዥ እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡ 

ሴት የሰላም አምባሳደሮቹ በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ በነበራቸው ቆይታም ከዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መምህራንና ሠራተኞች ጋር በሰላም ዙሪያ መክረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር ያሬድ ማሞ በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የሆነ የመማር ማስተማር መኖሩን ገልጸው የሚፈጠሩ ችግሮችን በመነጋገርና በመግባባት በመፍታት ላይ እንደሚገኙና ይህንንም ተግባር አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ነው ተናግረዋል፡፡ (ምንጭ፡የድሬዳዋ አስተዳደር መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)