ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 140 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎችን አነጋገሩ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ 13ኛውን የብሔር ብሔረሰቦች ቀንን በማስመልከት በዛሬው ዕለት ከመላው ሀገሪቱ የተውጣጡ 140 የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎችን በጽህፈት ቤታቸው ቅጥር ግቢ ተቀብለው አነጋግረዋል።

በዚህም ታዳጊዎች ኢትዮጵያዊነትን የሚያደምቁ የነገዋን ኢትዮጵያ የሚገነቡና የሚመሩ በመሆናቸው ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩ  በተጨማሪም ተማሪዎቹ ከመገለልና ልዩነትን ከማቀንቀን ይልቅ ሰፋ ያለ አመለካከትን፣ እርቅን፣ የአንድነትን፣ እና የትብብርን አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት መሥጠት እንደሚገባቸው  ተናግረዋል።

ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸው ጥበብ፣ ቋንቋ፣ ማንነት እና አገር በቀል ዕውቀት ባለቤት መሆናቸውን ከግምት ማስገባት ታላቅ ትምህርት እና ግንዛቤ ለመውሰድ እድል ይሠጣል ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትሩ ፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ ክብርና ማንነት ማሳየት በሚችል መልኩ ራሳቸውን እንዲገነቡ ለታዳጊዎች ያሳሰቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ልጆች ከጥላቻ መራቅ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

አሁን ላይ በሀገሪቱ እየታየ ያለውን ለውጥ ዳር በማድረስም የተሻለች ኢትዮጵያን እናስረክባቸኋለን ሲሉ ለታዳጊዎቹ ቃል ገብተዋል። (ምንጭ፡-ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)