ፎርብስ መፅሄት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን ከ2018 ተፅእኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ አካተተ

ፎርብስ መፅሄት ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን በፈረንጆቹ 2018 ዓመት ከዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች ዝርዝር ውስጥ ማካተቱ ተገለጸ።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ በፎርብስ መፅሄት በመመረጥ ከአፍሪካ ብቸኛዋ መሆናቸውም ነው የተገለጸው።

የፕሬዝዳንቷ ሹመት በሴቶች ላይ ወግ አጥባቂ አመለካከት ለሚንፀባረቅባት አገር እንደ አንዳች አስደማሚ ምልክት ሊቆጠር እንደሚችልና ለስርዓተ ፆታ መከበር አዎንታዊ ሚናው የጎላ መሆኑን ፎርብስ ጠቅሷል።

የ2018ቱ የዓለም 100 ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መዝገብ በስራቸው ፈርጥ ሊሆኑ የሚችሉ ተግባራትን ያከናወኑ፣ በፈጠራ ስራዎች የመጠቁ፣ ድምጻቸው የነበረን ልማድ በመዋቅራዊ ለውጥ ሊያሻሽል የሚችል ሁኔታን ያመቻቹ እና ተፅዕኖ የፈጠሩ ግለሰቦች የሚሰፍሩበት እንደሆነም ገልጿል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ እስካሁን በመፅሄቱ ከተካተቱ ጥቁር ተፅዕኖ ፈጣሪ ሴቶች መካከል በ97ኛ ቁጥር ላይ የተመዘገቡ ሲሆን በ20ኛ ተራ ቁጥር ላይ ኦፕራ ዊንፍሬ፣ በ50ኛው ቁጥር ላይ ቢዮንሴ ኖውልስ እንዲሁም እውቋ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ሴሪና ዊሊያምስ 79ኛ ላይ እንደሰፈሩ ካፒታል ቢዝነስ ድረ-ገጽ ጠቁሟል።

የጀርመኗ መራሂተ-መንግስት አንጌላ ሜርኬል፣ የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴሬሳ ሜይ፣ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ ኤም ኤፍ) ማኔጂንግ ዳይሬክተር ክርስቲን ላጋርድ፣ የጄኔራል ሞተርስ ዋና ስራ አስፈፃሚ ሜሪ ባሪ እና የቢል ኤንድ ሜሊንዳ ጌትስ ሊቀ-መንበር ሜሊንዳ ጌትስ ከተጽዕኖ ፈጣሪዎቹ መካከል ተካትተዋል።

ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅን ከአፍሪካ በስልጣን ላይ ያሉ ብቸኛዋ ሴት ፕሬዝዳንት ያለው ድረ-ገጹ ከዚህ ቀደም የአፍሪካ ህብረትን በመወከል በመንግስታቱ ድርጅት ቁልፍ ኃላፊነት ላይ መቆየታቸውንም አንስቷል።

አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች ባካሄዱት አስቸኳይ የጋራ ስብሰባ ባገኙት የሙሉ ድምጽ ድጋፍ የመጀመሪያዋ የኢትዮጵያ ሴት ፕሬዝዳንት ሆነው መመረጣቸው ይታወሳል።

ፕሬዚዳንቷ ላለፉት 30 ዓመታት በብሔራዊ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ በውጭ ግንኙነት ሥራ የካበተ ልምድ አላቸው።