“የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ኢትዮጵያዊያን ዘመኑ የሚጠይቀንን አብሮነታችንን የምናሳይበት በዓል ነው” ኢንጂነር ታከለ ዑማ

13ኛው የኢትዮጵያ የብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል በአዲስ አበባ ከተማ አስተናጋጅነት በአዲስ አበባ ስታዲየም አየተከበረ ነው።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ የዘንድሮ 13ኛውን የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ቀንን ለማክበር የእንኳን ደህና መጣችሁ እና የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

ኢንጂነር ታከለ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች በዓል ኢትዮጵያዊያን ዘመኑ የሚጠይቀንን አብሮነታችንን የምናሳይበት በዓል ነው ብለዋል፡፡

የዛሬው ቀን የለውጥ ጉዞን ወደ አዲስ ምዕራፍ የምናሻግርበት የሁሉም ኢትዮጵያውያን ቀን ነው ያሉት ምክትል ከንቲባው በዓሉ እየተከበረ ያለው በመላው አገራችን የእኩልነትና የአንድነት ችቦ በተለኮሰበት በአሁኑ ወቅት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ጊዜው ሁሉም ዜጎች አገሬ የሚሏትን ኢትዮጵያን ለመገንባት የምንሰራበት ነው ያሉት ኢንጂነር ታከለ ልማታችን ከግብ እንዲደርስ ካለፈው የበለጠ ትግል ይጠይቀናል ብለዋል፡፡

አሁንም ለውጡን ወደ ኋላ ለመመለስና ለመቀልበስ የሚፈልጉ የወዳደቁ አስተሳሰብ አራማጆች አሉ ያሉት ምክትል ከንቲባው ሁሉም ዜጎች ሀገሬ የሚለውን ህልም እውን ለማድረግ ነገን አሻግሮ የሚያይ ህዝባዊ አንድነት እና ጠንካራ ትስስር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

በዓሉ ኢትዮጵያዊ አንድነትን ወደ ታላቅ ከፍታ የምናሻገርበትና እኛም ይህንን ለማድረግ ቃል የምንገባበት ይሆናል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያን ከመነሻዋ አንስቶ አሁን ወደደረስንበት ከፍታ በተፃፈበትም ሆነ ባልተጻፈው ጉዞዎች እንዲሁም ቃላት የማይገልጻቸውን መስዋዕትነት ከፍለው ለዚህ ቀን ላደረሱት አባቶቻችን ታላቅ ክብርና ምስጋና ይድረሳቸውም ብለዋል በንግግራቸው፡፡

በሀገሪቱ ከጫፍ እስከ ጫፍ የጠለቀው ኢትዮጵያዊ አንድነት እንድጎላና በመላው ሀገሪቱ የተለኮሰው የሁሉም ዜጋ የእኩል ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ የሚገኘውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን አመሰግናለው ብለዋል፡፡

ለበዓሉ ድምቀት አስተዋጽኦ ያበረከቱትን አካላት ያመሰገኑት እንጂነር ታከለ በስነ ምግባር የምትታወቁ የሸገር ልጆች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጠናከር ላደረጋችሁት አስተዋጽኦ አመሰግናለሁ ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በበዓሉ ላይም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ አቶ ታገሰ ጫፎ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማን ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል እና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።