የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ኛው መደበኛ ጉባኤ በመቀለ ከተማ ከታህሳስ 7 እስከ 9 ድረስ ይካሄዳል

የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ተኛ መደበኛ ጉባኤዉን በመቀለ ከተማ ከታህሳስ 7 እስከ 9 2011 ዓ.ም ያካሂዳል፡፡

የተደራጀ የሴቶች ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለሁለንተናዊ ሃገራዊ ለዉጥ በሚል መሪ ቃል የሚካሄደዉን ጉባኤ አስመልክቶ የሚካሄደዉ ጉባኤ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን የኢህአዴግ ሴቶች  ሊግ ፅህፈት ቤት  ኃላፊ ወይዘሮ ሰአዳ ኡስማ በዛሬው ዕለት  በሠጡት መግለጫ ገልጸዋል ፡፡

ለሶስት ቀናት በሚቆየውና በተለያዩ መርሃ ግብሮች በሚጀመረው ጉባኤ በመክፈቻው ከ1000 እስከ 1500 የሚሆኑ ተሳታፊዎች እንደሚገኙ የተገለጸ ሲሆን በጉባኤው 700 የሊጉ አባላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዚህ ጉባኤ በዋናነት ሶስት አበይት አጀንዳዎች ላይ ውይይት እንደሚካሄድም በመግለጫው ተመልክቷል ፡፡ 

በሶስተኛው መደበኛ ጉባኤ ላይ የተቀመጡ አቅጣጫዎችን አፈፃፀም በመገምገም የቀጣይ የትኩረት አቅጣጫን ማስቀመጥ፣በሃገሪቱ እየታየ ያለዉን ለውጥ ለማስቀጠል አባላቱ ምን ማድረግ አለባቸው በሚለዉ ላይ በትኩረት ውይይት እንደሚደረግበት ተገልጿል ።

እንዲሁም በቀጣይ ሊጉን ሊመሩ የሚችሉ አመራሮችን መምረጥ የጉባኤው ሌላው የትኩረት ጉዳይ  መሆኑ  ተገልጿል፡፡