የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው ከኢንተርፖል ዋና ጸሃፊ ጀርገን ስቶክን ጋር ተወያዩ

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው ጣሰው ከዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት (ኢንተርፖል) ዋና ጸሃፊ ጀርገን ስቶክን ጋር ተወያይተዋል።

ኮሚሽነር ጀኔራል እንደሻው በዚህ ውይይታቸው የኢንተርፖል ለኢትዮጵያ የግብዓት፣ ስልጠና እና የቴክኖሎጅ እገዛ ለማድረግ በሚችልባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል።

የኢንተርፖል ደንብ በሚፈቅደው መሰረትም የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተጠርጣሪዎች የትም ሀገር ወንጀል ፈጽመው መደበቅ እንዳይችሉ ለማድረግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከድርጅቱ ዋና ጸሃፊ ጋር ተወያይተዋል።

ኢትዮጵያ የኢንተርፖል አባል ከሆነች ከ60 ዓመት በላይ ያስቆጠረች መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነር ጀኔራሉ ከ194 አባል ሀገራት ጋር ግንኙነት ያላት መሆኑንም አስረድተዋል።

አሁን ላይ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ከሁሉም ሃገራት ጋር መልካም ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባም ገልጸዋል።

የኢንተርፖል ዋና ጸሃፊ ጀርገን ስቶክን በበኩላቸው ኢትዮጵያ አሁን የጀመረችውን የእድገት ጎዳና በማድነቅ የተለያዩ ስልጠናዎችን ለመስጠትና የፎረንሲክ ምርመራው በቴክኖሎጅ የታገዘ እንዲሆንና ማንኛውም ሰው ወንጀል ፈጽሞ የትም መደበቅ እንደማይችል ተናግረዋል። (ምንጭ፡- የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን)