ጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ህልፈት የተሰማቸውን ሐዘን ገለጹ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በቀድሞ ፕሬዚዳንት ህልፈተ ህይወት  ምክንያት የተሰማቸውን ሀዘን ገለጹ፡፡

ከ1994 እስከ 2006 ዓም የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዜና እረፍት በመስማቴ  በኢፌዴሪ መንግሥት እና በራሴ ስም የተሰማኝን ጥልቅ ኀዘን ለመግለጽ እወዳለሁ ብለዋል ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ።

ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የኢፌዲሪ መንግሥትን በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ፣ በልዩ ልዩ ኃላፊነት ለሀገራቸው ረዥም ዘመን የሠሩ፣ በዕውቀታቸውና በሞያቸው ለሕዝባቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የሰጡ፣ የታታሪነት፣ የቅንነትና፣ የሕዝባዊ አገልግሎት ሰጭነት ተምሳሌት እንደነበሩም አስታውሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክትም  በፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ዕረፍት ምክንያት  ጥልቅ  ሃዘን ለተሰማቸው ቤተሰቦቻቸውና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መጽናናትን እመኛለሁ ብለዋል።

መንግሥታዊ የቀብሩን ሥነ ሥርዓት የሚያስፈጽም ኮሚቴ የተቋቋመ መሆኑም  ተመልክቷል ።

የቀድሞ ፕሬዚደንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስን በተመለከተም አስፈላጊውን መግለጫ እንደሚሰጥም ተገልጿል ። (ምንጭ: ጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት )