ወደ ቤተመንግስት ካመሩት የመከላከያ ኮማንዶ አባላት ውስጥ 66ቱ በወታደራዊ አመጽ ጥፋተኛ ተባሉ

በመስከረም 30፤2011 ወደ ቤተመንግስት ካመሩት የመከላከያ ኮማንዶ አባላት ውስጥ 66ቱ በወታደራዊ አመጽ ጥፋተኛ ሆነው  በመገኘታቸው ቅጣት እንደተላለፈባቸው ተገለጸ፡፡

የመከላከያ ወታደራዊ ፍትህ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮሎኔል መሸሻ አረጋ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮን በጥብቅ ድስፒሊን በመወጣት የሚታወቅ ነው ብለዋል ።

 ሆኖም በመስከረም  30  ቀን የተወሰኑ የኮማንዶ አባላት በወታደራዊ አመጽ  በመሳተፍ  በሠራዊቱ አባላት ታሪክ ጥቁር ነጥብ የጣሉ መሆናቸውን አብራርተዋል ፡፡

ከእርምጃው ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ሲናፈሱ የነበሩ ወሬዎች መከላከያን የማይገልጹ መሆናቸውና መከላከያ በህግ የተቋቋመ ለሀገር ደህንነት የሚሰራ እንደሆነ ሊታሰብ እንደሚገባም ኮሎኔል መሸሻ አሳስበዋል፡፡

የወታደር አቃቤ ህግ የሆኑት ሻምቤል ኃይለማሪያም ማሞ ወታደሮች እምቢተኛ በመሆን፣ ትዕዛዝ አልቀበል በማለት እና ወታደራዊ ሥርዓትን በማወክ ክስ ጥፋተኛ መባላቸውን ገልጸዋል፡፡

በጥፋታቸው መሠረትም አጥፊዎቹ  ከ5 እስከ 14 ዓመት ድረስ የተፈረደባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የወታደራዊ ተከላካይ ጠበቃ ሻለቃ ደሣለኝ ዳቃ በበኩላቸው ችሎቱ ግልጽ በሆነ አዳራሽ እንደተካሄደና የተከሳሾቹን ህገመንግስታዊ መብታቸውን የጠበቀ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም ይግባኝ ለማለት በሂደት ላይ መሆናቸውን ጠበቃው አስታውቀዋል፡፡