የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በመቐለ እየተካሄደ ነው

የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ 4ኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በመቐለ ከተማ መካሄድ ጀምሯል።

በጉባዔ መክፈቻ  የኢህአዴግ ሴቶች ሊግ ሊቀመንበርና የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂ እና የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፂሆን ገብረሚካኤል ተገኝተዋል።

በዚህ ወቅት ንግግር ያደረጉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል፥ ላለፉት ሁለት አመት ተኩል በተለያዩ አቅጣጫዎች ከባድ ትግል መደረጉን እና በአሁን ሰአት  ኢትዮጵያ በአስጊ እና በአጓጊ ሁኔታዎች መከበቧን ተናግረዋል።

እንደ ሀገር የሚታዩ ተግዳሮቶችን መቅረፍ እንዲቻል ሴቶች የበኩላቸውን አስተዋፆኦ ሊያደርጉ እንደሚገባ ነው ወይዘሮ ሙፈሪያት ያሳሰቡት።

ሴቶች ተፈጥሯዊ ባህሪያችን ለሰላም የቀረበ ነው ያሉት ወይዘሮ  ሙፈሪያት ካሚል ህዝብ እንደ ህዝብ ጥላቻ እንደሌለበትም ተናግረዋል።

መቼም ቢሆን ሴቶች ለሀገራዊ ሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ በመንቀሳቀስ ሀገሪቱ ከፊቷ የተደቀነባትን ተግዳሮቶች ማፅዳት እንደሚገባቸው ለጉባኤው ተሳታፊዎች አሳስበዋል።

ለሶስት  ተከታታይ ቀናት በሚቆየው ጉባኤ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ በተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች ተሳታፊ ናቸው።

በዚህ ጉባዔ ድርጅቱ ለሴቶች የተሠጠውን ትኩረት አጠናክሮ የሚያስቀጥል አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የተደራጀ የሴቶች ተሳትፎ ለሀገራዊ ለውጡ የጎላ ፋይዳ እንዳለው በማሰብ  ኢህአዴግ በሴቶች ዙሪያ እያደረገው ላለው እንቅስቃሴ ጉባኤው ተጨማሪ ጉልበት  ይኖረዋል ተብሏል።(ኤፍቢሲ)