በኢትዮጵያ ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

በኢትዮጵያ ህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡

ከዋልታ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌዴራል ፖሊስ ፈጥኖ ደራሽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኮማንደር አይሳ ዳመና እንደገለጹት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ሀገር ውስጥ ሲገባና ከገባ በኋላ በቁጥጥር ስር እየዋለ ያለው ህገወጥ የጦር መሳሪያ የሀገሪቱን ሰላም ችግር ላይ የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይ በህገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር ላይ እየተሳተፉ ያሉት የከባድ እና የቦቲ መኪና አሽከርካሪዎች በመሆናቸው ባለንብረቶቹ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

በአብዛኛው እየተያዙ ያሉት መሣሪዎች ቱርክ ሰራሽ በመሆናቸው ከጀርባ ማን እንዳለ የማጣራት ሥራ በስፋት እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ኮማንደር አይሳ የህገ ወጥ ማሳሪያ ዝውውር እስከ 15 ዓመት እንደሚያስቀጣ ገልጸዋል፡፡

ከዚህው ጋር በተያያዘ 58 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራቸው እየተካሄደ ሲሆን ህብረተሰቡ ችግሩን ለመከላከል ከመንግስት ጎን እንዲቆም ኮማንደሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሌላ በኩል ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በአገር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት በተመለከተ ሰፊ የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ተጀምሯል ያሉት ኮማንደር አይሳ በዚህ ተግባር ላይ መሳተፍ ሀገርን ከፍተኛ ችግር ላይ የሚጥል በመሆኑ ሁሉም እጁን እንዲሰበስብ አሳስበዋል፡፡

ከዚህ በሻገር የክልል ልዩ ኃይሎች መካከል አንዳንዶቹ የሚታጠቁት መሣሪያ እንደመንግሥት አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ይህንን በተመለከተ ሰፊ ሥራዎች መሰራት እንዳለበትም ግንዛቤ መወሰዱ ተመልክቷል፡፡

በህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተለያየ መልኩ እየገቡ በመሆናቸው በድንበርና አዋሳኝ አካባቢዎች በሚፈጠር ግጭት ላይ እየዋለ ሰፊ ችግር እየፈጠረ መሆኑንም ኮማንደሩ ገልጸዋል፡፡

በግጭቱ ወቅትም ፖሊስና መከላከያ ኃይል ግጭቱን ለማብረድ በሚወስዱት እርምጃ ላይ የህገወጥ ጦር መሣሪያ ዝውውር አላስፈላጊ መስዋዕትነት እያስከፈለ ሰላም የማስከበርን ሥራ አስቸጋሪ እያደረገ መሆኑን ኮማንደር አይሳ ዳመና አስታውቋል፡፡