ምክር ቤቱ የአንድ ቀን ብሄራዊ የሀዘን ቀን አወጀ

የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ ከዚህ አለም በሞት መለየትን አስመልክቶ የአንድ ቀን  የብሄራዊ የሃዘን ቀን አወጇል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 12 መደበኛ ስብሰባው ላይ የብሔራዊ የሃዘን ቀን ማወጁን ያስታወቀው።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአዋጅ ቁጥር 653/2009 አንቀፅ 11 ያስቀመጠው ደንብን ተከትሎ ነው በመላው ሀገሪቱ የ1 ቀን ብሄራዊ ሀዘን የታወጀው ።

ምክር ቤቱ ባወጀው የሃዘን ቀን መሠረትም በነገው ዕለት ወይም ታህሳስ 10 ቀን 2011 ዓ.ም ብሄራዊ የሀዘን ቀን ሆኖ ይውላል።

በሃዘን ቀኑ ሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎችና ቆንስላ ጽህፈት ቤቶች ለአንድ ቀን የሀገሪቱ ሰንደቅ አላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ወስኗል።

በባህር ላይ የሚገኙ  የኢትዮጵያ የሆኑ መርከቦችም ከነገ ጀምሮ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. ባንዲራ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ይደረጋል ።