የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብብሰባ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳለፈ።

ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ስፔስ ፖሊሲ፣ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን እንደገና ለማቋቋም በቀረበው ረቂቅ አዋጅ፣ የሕገመንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም ረቂቅ አዋጅ፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ረቂቅ አዋጅ ላይ  ተወያይቶ አፅድቋል።

በዚህም የኢትዮጵያ ስፔስ ፖሊሲን ስራ ላይ እንዲውል ያፀደቀ ሲሆን፥ ሦስቱን ረቂቅ አዋጆች እንዲፀደቁ ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።

ምክር ቤቱ መጀመሪያ የተወያየበት አጀንዳ በኢትዮጵያ ስፔስ ፖሊሲ ላይ ሲሆን፥ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የስፔስ ፖሊሲ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረቡም ተጠቅሷል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤትም በዝርዝር ተወያይቶ ማስተካከያዎችን በማከል ስራ ላይ እንዲውል ወስኗል።

በሁለተኛ የቀረበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን በተመለከተ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ነው።

በዚህም የዜና አገልግሎቱ እንደ ሀገራዊ ዜና አገልግሎት የተረጋገጠ መረጃ ለመስጠት እና ተወዳዳሪ አቅም እንዲገነባና ተቋማዊ የአሰራር ነጻነት እንዲኖረው ለምክር ቤቱ ውሳኔ መቅረቡ የተገለጸ ሲሆን ፥ ምክር ቤቱም አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲላክ ወስኗል።

ሦስተኛው አጀንዳ የሕገመንግስትና ፌደራሊዝም አስተምህሮ ማዕከልን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ሲሆን፥ ይህም ዜጎች በህገመንግስታዊና በፌደራሊዝም ላይ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት እና የመቻቻል ባህልን ለማጎልበት ሀገራዊ እሴቶችን ለማዳበር ያላቸው ሚና የላቀ በመሆኑ የቀረበ ነው ተብሏል።

ረቂቅ አዋጁንም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረበ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም ማሻሻያዎችን በማከል ወደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ልኳል።

ምክር ቤቱ በመጨረሻ የተወያየበት የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን በተመለከተ የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ነው።

በዚህም የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የዜጎችን ለህጋዊ አላማ የመደራጀት መብት ለማረጋገጥ እና በሀገሪቱ ልማትና ዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ያላቸው ሚና እንዲጎለብት ለማድረግ የተመቻቸ ምህዳር ለመፍጠር የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶችን ተጠያቂነትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲቻል በማሰብ ነው ተብሏል።

ረቂቅ አዋጁን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረቡ የተጠቀሰ ሲሆን፥ ምክር ቤቱም በአዋጁ ላይ ተወያይቶ ማስተካከያዎችን በማከል ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ ወስኗል ።(ምንጭ:የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት )