በህገ-ወጥ መንገድ 4583 ካ.ሜ መሬት ለባለሃብቶች ያስተላለፈው ኃላፊ ለከንቲባ ጽህፈት ቤት በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ዋለ

በህገ-ወጥ መንገድ 4 ሺህ 583 ካ.ሜ መሬት ለባለሃብቶች ያስተላለፈው ኃላፊ ለከንቲባ ጽህፈት ቤት በደረሰ ጥቆማ መሰረት በቁጥጥር ስር መዋሉን የከንቲባ ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 በተለምዶ አጃንባ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ የመሬት አስተዳደር የሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ከሶስት የክፍሉ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር መሬት ባንክ በኮድ ቁጥር 79 ገቢ የተደረገን ባዶ ቦታ የድርጅት በማድረግ እንዳስተላለፈ ነው የተገለጸው፡፡

ግለሰቡ መረጃውን ማዛባትና ለግለሰቦች ካርታ አዘጋጅቶ በመስጠት የህዝብን ውስን ሃብት ለግል ጥቅም በማዋል መንግስት ሊያገኘው የሚገባውን 12 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር እንዳሳጣ ተገልጿል፡፡

የመሬት አስተዳደር የሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊ የሆነው ግለሰብ ከተጠቀሱት ባለሃብቶች ጋር በግል በፈጠረው ያልተገባ ቁርኝት አንደኛውን ባለሃብት 600ሺህ እና ሁለተኛውን 400 ሺህ ብር የሊዝ ዋጋ በማስከፈል በድርጅት ስም የመሬት ባንክ ንብረት የሆነውን 4 ሺህ 583 ካሬ ሜትር አጥር የሌለው ቦታ አስተላልፏል፡፡

ይህን የታዘቡት የአከባቢው ነዋሪዎች የከተማ አስተዳደሩ በዘረጋው የጥቆማ መስጫ ቁጥር በመጠቀም ለከንቲባ ጽህፈት ቤት ጥቆማ እንዳደረሰ ነው የከንቲባ ጽህፈት ቤት ያስታወቀው፡፡

ጽህፈት ቤቱ ጥቆማው እንደደረሰ አጣሪ ግብረኃይሉን በቀጥታ ወደ ተጠቀሰው ክፍለ ከተማ በመላክ ከመሬት ማኔጅመንት ቢሮ ጋር በመተባበር ባደረገው የማጣራት ስራ መሬቱ ያለ አግባብ መሠጠቱን እና በሰነድ አልባ ዴስክ ኃላፊው የተፈረመው ካርታም ትክክለኛ አለመሆኑን ካረጋገጠ በኃላ ተጠርጣሪዎችን በህግ ቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳያቸውን በማጣራት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የከተማችን ነዋሪዎች አሁንም የከተማ አስተዳደሩ የጀመረውን ህግ የማስከበር ተግባር በመደገፍ ለውጡን ለማደናቀፍ የሚሯሯጡ አመራሮችን፣ ባለሙያዎችን እና ግለሰቦችን በመጠቆም ለውጡን እንዲደግፉ ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)