ምክር ቤቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን አፀደቀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅን አፀደቋል።

ምክር ቤቱ በዛሬው እለት ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባው ነው ብሄራዊ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጁን ያጸደቀው።

በመደበኛ ስብሰባውም የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ እና የህግ፣ ፍትህና ዲሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርትና የውሳኔ ሃሳብ ዙሪያ ውይይት አድርጓል።

በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ሀሳብ እና አስተያየት ያነሱ ሲሆን፥ ማነው የተጣላው ማነው የሚታረቀው፣ ኮሚሽኑ ነፃ እና ገለልተኛ ነው የሚባለው እስከ ምን ድረስ ነው፣ የአዋጁ ቃላት አጠቃቀም ቢታዩ የሚለው ላይ አስተያየት አቅርበዋል።

ይቅርታ ከፍትህ በላይ አርኪ ነው ያሉት የምክር ቤቱ አባል፥ አሰራሩ ግን ችግር ፈቺ በሆነ መንገድ መታየት እንዳለበትም ነው የገለፁት።

እርቅ መጀመር ያለበት ከዚሁ ከምክር ቤቱ መሆን አለበት ያሉት የምክር ቤቱ አባል፥ የኮሚሽኑ ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቢፀድቅ መልካም ነውም ብለዋል።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሰባቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በተነሱ አስተያየቶች ላይ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ኮሚሽኑ በህብረተሰቡ ዘንድ የሚነሱ ስሜቶችን ምንጭ የማጥራት እና የአብሮነት እሴቶችን የማሳገድ ስራዎችን የሚሰራ ነው ብለዋል።

የኮሚሽኑ ዋነኛ አላማም በህብረተሰቡ ዘንድ ያሉ የቅሬታ ምንጮችን በማጥራት የውሳኔ ሀሳብ አቅርቦ የእርቅ ስርዓት መፈፀም መሆኑን ገልጸው ከዚህ የዘለለ ሀላፊነት የለውም ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ ተጠሪነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሆኖ ነፃ እና ገለልተኛ እንዴት ሊሆን ይችላል በሚለው ላይም በሰጡት ማብራሪያ፥ ይህ ሊያጠያይቅ አይገባም ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑን አባላት በእጩነት ያቀርባሉ እንጂ እጩዎቹን የሚያፀድቀው ምክር ቤቱ በመሆኑ ማን አባል ሊሆን ይገባል ማን አይሆንም የሚለው ላይ ምክር ቤቱ እንደሚወስንም አስታውቀዋል።

ከዚህ ባለፈም ምክር ቤቱ የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ስራውን በሚሰራበት ወቅትም ከማንኛውም ጫና ነፃ እንዲሆን የህግ ድጋፍ የሚሰጠው መሆኑንም አስረድተዋል።

ምክር ቤቱ ብሄራዊ የዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ለማቋቋም የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተወያየ በኋላ በ1 ተቃውሞ፣ በ1 ድምጸ ተአቅቦ እና በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።