የኦሮሚያ ክልል በሙስና የተወሰዱ ንብረቶችን ለማስመለስ የህግ ክፍተት እንዳለ አስታወቀ

የኦሮሚያ ክልል በሙስና የተወሰዱ ንብረቶች ለማስመለስ የህግ ክፍተት እንዳለ አስታወቀ።

በሀገር አቀፍ  ደረጃ እየተካሄደ ካለው ፀረ ሙስና ዘመቻ ጎን ለጎን ትልቅ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን የኦሮሚያ ክልል የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አበበ ከበደ  ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ  በክልሉ የተደራጀ ሌብነት መኖሩን የገለፁ ሲሆን፥  ችግሩን ለመቅረፍ ግንዛቤ የመፍጠር ስራና በማስረጃ ተደግፈው  የቀረቡትን ደግሞ በህጋዊ መንገድ እንዲጠየቁ የማድረግ ስራ በሰፊው እየተሰራ ነው ብለዋል።

በክልሉ የተጭበረበረ ሰነድ በመጠቀም እና በኢንቨስትመንት ስም የመንግስት ገቢን እስከ ማስቀረት የሚደርስና ሌሎች ተመሳሳይ ወንጀሎች እንደሚፈፀሙ ተናግረዋል።

በዚህም በተሰራው ስራ 16 ነጥብ 119 ቶን ብረት እና 6 ሺህ  ሄክታር ያላግባብ የተያዘ መሬት ለመንግስት ገቢ ተደርጓል።

ህገ ወጥ የመሬት ወረራ ፣ ህገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ሥልጣንን ያላግባብ መጠቀም እና ሌሎች ወንጀሎች በስፋት ይስተዋላሉ ተብሏል።

የመንግስት በጀት ላልተሰራ ፕሮጀክት እንደተከፈለ አድርጎ ማቅረብ ፣ ያልተስተካከለ እና ለሙስና የተጋለጠ የግዥ ስርዓትም በክልሉ ከሚፈፀሙ የሙስና ወንጀሎች ውስጥ የሚጠቀሱ ናቸው።

የወንጀል አይነቱ በተደራጁ አካላት መፈጸም ደግሞ ስራውን ውስብስብ አድርጎታል ነው ያሉት።

በእርዳታ እና ብድር መልኩ ከተለያዩ የውጭ ተቋማት የሚገኙ የበጀት አይነቶች በከፍተኛ ደረጃ ለዚህ ችግር ተጋላጭ እንደሆኑ ተደርሶበታል ብለዋል ኮሚሽነሩ።

እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍም  ኮሚሽኑ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ኮሚሽነር አበበ  በቀጣይም  የመንግስት ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ በክልሉ የሚገኙ የመንግስት ልማት ድርጅቶች የሚፈተሹ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሌላ በኩል በዝርፊያ መልኩ የተወሰደውን ሀብት ለማስመለስ የህግ ክፍተቶች መኖራቸውን በማንሳት ይህም ለወደፊቱ መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ኮሚሽኑ በአሁኑ ጊዜ በክልሉ በሚገኙት ስምንት ቅርንጫፎች የተደራጀ ፀረ ሙስና  ትግል እያካሄድኩ ነው ብለዋል።(ኤፍ.ቢ.ሲ)