ቪዠን ኢትዮጵያ በድህረ- ግጭት ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችን አቀረበ

ቪዠን ኢትዮጵያ የተባለ በኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች የተቋቋመ ማህበር በኢትዮጵያ  እየተከሰቱ  ባሉት  ግጭቶችና ከድህረ  ግጭት ጋር  በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩሩ ጥናቶችን ለሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት  ሚኒስቴር አቀረበ።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከቪዠን ኢትዮጵያ ማህበር ጋር  በመተባባር በዛሬው  ዕለት ባዘጋጀው ጉባኤ ላይ   በአገሪቱ  እየተፈጠሩ  ባሉት  ግጭቶች ላይ  የሚያተኩሩ  21  የሚደርሱ ጥናቶችን እያቀረበ ይገኛል  ።

የቪዠን ኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር  ጌታቸው በጋሻው እንደገለጹት የጉባኤው ዋና ዓላማ በአገሪቱ እየመጣ ያለውን ለውጥ ይበልጥ  ወደ መሬት ወርዶ ተግባራዊ እንዲሆን ፤ቪዠን ኢትዮጵያ ያካሄዳቸው ጥናቶች ትልቅ ግብዓት ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።

በዛሬው ዕለት ቪዠን ኢትዮጵያ ያቀረባቸው ጥናቶች ሳይንሳዊ እውነቶችን መሠረት በማድረግ የተሠሩና  ፖለቲካዊ ፣ ማህበረሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ታሪካዊ ጉዳዮችን  የዳሰሱ መሆናቸውን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል ።

ቪዠን ኢትዮጵያ አገራቸውን ለማገልገል ዕድል ያላገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በተሠማሩበት ዘርፍ  ለአገራቸውና ለዜጎቻቸው በነጻ አስተሳሰብ  እውቀታቸው ሥራ  ላይ እንዲያውሉ የሚያስችል ማህበር መሆኑም  ተገልጿል ።  

በዛሬው ዕለት በኔክሰስ ሆቴል እየተካሄደ ባለው ጉባኤ  የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ወልደማሪያምን ጨምሮ የሚመለከታቸው  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ።