መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ ሚስጥራዊ የማሰቃያ እስር ቤት ማግኘቱን አስታወቀ

መርማሪ ፖሊስ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሲፈፀምበት የነበረ ተጨማሪ ሚስጥራዊ የማሰቃያ እስር ቤት ማግኘቱን ለፍርድ ቤት አስረዳ።

መርማሪ ፖሊስ በቀድሞ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሁለት ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች በነበሩ ማእሾ ኪዳኔ እና ሀዱሽ ካህሳይ የምርመራ ሂደት ላይ በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛው የወንጀል ችሎት ቀርቦ ማብራሪያ ሰጥቷል።

ተጠርጣሪ ማእሾ ኪዳኔ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት በተለያዩ ሀላፊነት ሲሰሩ በነበረበት ወቅት የተሰጣቸውን ስልጣን ወደጎን በመተው በዋና ወንጀል አድራጊነት ነው መጠርጠራቸው ይታወቃል።

ተጠርጣሪው አሁን ካልተያዙት የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የቀድሞ ሀላፊ አቶ ጌታቸው አሰፋ ጋር በመመሳጠር በህገ ወጥ መንገድ በወቅቱ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የነበሩ ግለሰቦች ላይ ድብደባና ስቃይ እንዲሁም አስነዋሪ ተግባራትን በመፈፀም እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዳይገናኙና ፍርድ ቤት እንዳይቀርቡ የሚለውም ከተጠረጠሩበት የወንጀል ድርጊት ውስጥ ተጠቃሽ ነው።

እንዲሁም ከሚያገኙት ገቢ በላይ ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት አፍርተው መገኘታቸውም ነው የተገለፀው።

2ኛ ተጠርጣሪ አቶ ሀዱሽ ካህሳይ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ሲሰሩ በቁጥጥር ስር ባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ የሰብአዊ መብት ጥሰት ወንጀሎች እንዲፈፀሙ በማድረግ፣ ወንጀሉ መፈፀሙን እያወቁ ለህግ አካል ባለማቅረብ እና ከሚያገኙት ገቢ በላይ ምንጩ ያልታወቀ ከፍተኛ ሀብት አፍርተው ተገኝተዋል በሚል ነው የተጠረጠሩት።

ፖሊስ ከዚህ ቀደም በተሰጠው የምርመራ ጊዜ ወቅት ያከናወናቸውን ስራዎችም ለፍርድ ቤቱ ያስረዳ ሲሆን፥ በዚህ ወቅትም ከአምስት ሰዎች ተጨማሪ የቃል ምስክር መቀበሉን አስታውቋል።

ሲሰሩበት ለነበሩበት መስሪያ ቤትም የነበሩበትን የስራ ሀላፊነት ለመለየት ደብዳቤ ልኮ ውጤት መቀበሉንም ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

በተጨማሪም ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ሚስጥራዊ የማሰቃያ እስር ቤቶች በተጨማሪ አንድ አዲስ ሚስጥራዊ የማሰቃያ እስር ቤት ማግኘቱንም አስታውቋል።

መርማሪ ፖሊስ ተጨማሪ የምስክር ቃል መቀበል፣ የተጎዱ ዜጎችን የህክምና ውጤት መቀበል፣ ለመስሪያ ቤቶች የተጻፉ ደብዳቤዎችን ማሰባሰብ እና የምርመራ ቡድን በማቋቋም በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች ከሚገኙ ተጎጂዎች የቃል ምስክርነት መቀበል እንደሚቀረው ገልጿል።

ለዚህም ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ እንዲሰጠው ለፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 10ኛው የወንጀል ችሎት ጠይቋል፤ ፍርድ ቤቱ መርማሪ ፖሊስ ከጠየቀው ውስጥ የ10 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቅዷል። (ኤፍ.ቢ.ሲ)