አቶ አበበ አበባየሁ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ተሾሙ

አቶ አበበ አበባየሁ የኢትዮጵያ ኢንቨንስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር  በመሆን በጠቅላይ ሚንስትር ዶክተር አብይ ተሾመዋል፡፡

አቶ አበበ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር  ሆነው የተሾሙት በቅርቡ አምባሳደር በመሆን የተሾሙትን አቶ ፍፁም አረጋን በመተካት ነው ፡፡

አቶ አበበ ሹመቱን ተከትሎ በትዊተር ገፃቸው ባሰፈሩት መልዕክት  ሀገርን ለማገልገል መብቃት ትልቅ ክብር  በመሆኑ  ለዚህ ሥራ  ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

አዲሱ ኮሚሽነር በዓለም አቀፍ  ደረጃ  ከፍተኛ ውድድር ባለበት ኢትዮጵያን ተመራጭ የኢንቨስትመት መዳረሻ የማድረግ ሥራን  በብቃት ለመወጣትም  እንደሚሠሩ ተናግረዋል ፡፡

አቶ አበበ አበባየሁ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በህግ ትምህርት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማዕረግ ያገኙ ሲሆን ሁለት የማስተርስ ዲግሪ ከደቡብ አፍሪካና ከእንግሊዝ አግኝተዋል። ከዚህ ቀደም በኮሚሽኑ በምክትልነት ማገልገላቸውም ተነግሯል፡፡

አዲሱ ኮሚሽነር የግሉን ዘርፍ በማሳደግ፣በኢኮኖሚ ፓሊሲ፣ በአለም አቀፍ የንግድና ኢንቨስትመንት ስምምነት እና በማስተማር የካበተ ልምድ አላቸው ተብሏል፡፡

አቶ አበባ የኢንቨስትመንት  ኮሚሽን በምክትል ሀላፊነት ከመሆናቸው በፊት የአለም ባንክ አካል በሆነው አለም አቀፉ የፋይናስ ኮርፖሬሽን ሲሰሩ  እንደቆዩ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡