ኢንጅነር ታከለ ኡማ አገልግሎት መስጠት ያቆመውን የሰንዳፋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክትን ገበኙ

ኢንጅነር ታከለ ኡማ እና የከተማዋ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች አገልግሎት መስጠት ያቆመውን የሰንዳፋ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክትን በትላትናው ዕለት ገብኝተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ባለበት የኦፕሬሽናል ችግር ምክንያት ለከፍተኛ ጉዳት እየተጋለጡ ያሉትን የአካባቢውን ነዋሪዎች ከሳይንስ እና ኢኖቬሽን ሚንስትሩ ዶክተር ጌታሁን መኩሪያ ጋር በመሆን አወያይተዋል፡፡

የአካባቢው አርሶአደሮችም ከቆሻሻው የሚለቀቀው ፍሳሽ ማሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ማውደሙን እና ወደ መኖሪያ ቤታቸው ጭምር በመግባት ለከፍተኛ የጤና ችግር እየተጋለጡ እንደሚገኙ አንስተዋል።

ከህብረተሰቡ ለተነሱ ቅሬታዎች ምላሽ የሰጡት ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ የከተማ አስተዳደሩ በፕሮጀክቱ ምክንያት እርሻቸው ላይ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች በቂ ካሳ እንደሚከፈል እና እስከ አሁን በአከባቢው የተከማቸውን የቆሻሻ ችግሮቹን በሳይንሳዊ መንገድ ለመቅረፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከዚህ በኋላ የትኛውንም አይነት ቆሻሻ በአከባቢው እንደማይጥል ለአርሶአደሮቹ ቃል ገብተዋል፡፡

ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ፕሮጀክቱ ለ8 ወር ብቻ አገልግሎት ከሰጠ በኋላ ከአካባቢው ነዋሪዎች በደረሰበት ተቃውሞ ምክንያት ከሁለት አመት በፊት አገልግሎት ማቆሙ ይታወሳል። (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)