በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች የፍትህ ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባ አመላካች መሆናቸው ተገለጸ

​​​​​​በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ችግሮች የፍትህ ስርዓቱን ማጠናከር የሚያስፈልግበት ጊዜ መሆኑን የሚያመለካቱ ስለመሆናቸው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ ገለጹ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባዔ ሦስተኛ ዓመታዊ ስብሰባውን ያካሄደ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ህዝቡ በፍርድ ቤቶች ላይ ያለው እምነት እየቀነሰ መምጣቱን የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ አንስተዋል።

ለዚህም ደግሞ ስለዳኝነት ነጻነትና ገለልተኛነት በመንግስት ኃላፊዎችም ሆነ በህብረተሰቡ ዘንደ በቂ ግንዛቤ ያለመያዝና ዳኞች ተጠያቂ የሚሆኑበት ግልጽ መመዘኛ ያለመኖር እንደምክንያት ተጠቃሾች ናቸው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የህግ የበላይነትትን መጣስ፣ የዳኝነት ስርዓቱ ውስጥ ጣልቃ መግባትና ፍትህ መጓደል እየተስተዋ ካሉ ችግሮች ውስጥ ይጠቀሳሉ።

ይህንን በመረዳት መንግስት ለዳኝነት ዘርፍ ከወትሮው የተለየ ትኩረት መስጠቱን ያወሱት ፕሬዚዳንቷ፤ ይህን መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የፍርድ ቤት አመራር አባላት፣ ዳኞችና ሌሎችም ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ አመልክተዋል።

የክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶች በክልላቸው በዳኝነት ስርአቱ ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችና እየተሰሩ ያሉ ተግባራትን አቅርበዋል።

በዚህም የጋምቤላ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ኦባንግ ኡጅሉ፣ የሶማሌ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ አብዱላሒ ሰኢድ፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ደሳ ቡልቻ እና የትግራይ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ዶክተር ፋና ሃጎስ ተገኝተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቶቹ ቀደም ሲል በፍትህ ስርዓቱ ላይ ጣልቃ ገብነት ይስተዋልበት እንደነበር ጠቅሰው፤ አዲስ የማደራጀት ተግባር እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ በፍትሀ ስረዓቱ ውስጥ ነጻነት፣ ተዓማኒነት፣ ግልጸኝነት እንዲሁም በቴክኖሎጂ መደገፍ በትኩረት የሚሰራባቸው ነጥቦች መሆናቸውን አብራርተዋል።

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉባኤ የፌዴራል ፍርድ ቤት አመራር አባላትን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችንና የሁሉንም ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንቶችን በአባልነት የያዘ ነው።

ጉባኤው በዓመት አንድ ጊዜ መካሄድ እንዳለበት በህግ ቢቀመጥም ባለፉት 27 ዓመታት የተካሄደው ሁለት ጊዜ ብቻ መሆኑ ተገልጿል። (ኢዜአ)