ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ አቻቸው ጋር በሁለትዮሸ እና በአከባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያዩ

የኢፌዴሪ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ከሱዳኑ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቅፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አል ድሪር ሙሀመድ ጋር በሁለትዮሸ እና በአከባቢያዊ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ባደረጉት ንግግር ''ሱዳን በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጣት አገር ናት'' ብለዋል።

ሁለቱ አገሮች ለሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ፍላጎት መሳካት ቅድሚያ ሰጥተው እንደሚሰሩና የሁለቱ አገሮች ህዝቦች መፃኢ ዕድልም ተመሳሳይ መሆኑን የገለጹት ዶክተር ወርቅነህ በሁለቱ አገሮች መካከል በትብብር ለመስራት የሚያስችሉ በርካታ ያልተነኩ እምቅ እድሎች መኖራቸውንና ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ የሁለቱ አገሮች መሪዎች በቁርጠኛነት እንደሚሰሩ ተናግረዋል። 

''በሁለቱ አገሮች መካከል በከፍተኛ ደረጃ የተደረጉ የፖለቲካ ምክክሮች ሁለቱ ወገኖች ከፊት ለፊታቸው ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር እና ለህዝባቸው ጥቅሞች በጋራ ተጠቃሚነት ላይ በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን ማሳያ ነው'' ብለዋል።

የሱዳን የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ዶክተር አል ድሪር ሙሀመድ በበኩላቸው ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች ያሉ ሲሆን በአካባቢያችን እና በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ የጋራ ግንኙነታችንን ለማጠናከር እንሰራለን" ብለዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የሚመራው አዲስ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ለውጥ ሱዳን እንደምታደንቅም ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በግንቦት ወር 2010 ዓ.ም በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት በተመሳሳይ ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሳን አልበሽር በቅርቡ በኢትዮጵያ ባደረጉት ጉብኝት እንዲሁም ባለፈው ሳምንት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሱዳን ባደረጉት ጉብኝት የሁለቱን አገሮች ወንድማማች ህዝቦች ፍላጎት ለማሳካት በጋራና በትብብር ለመስራት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወቃል። (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)