የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አዳዲስ ሹመቶችን ሰጠ

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት ባካሄደው አራተኛ አስቸኳይ ጉባኤ አዳዲስ ሹመቶችን አጸደቀ፡፡

ከተሿሚዎች መካከል የምክር ቤቱን አፈ-ጉባኤ በአዲስ የተኩ ይገኙበታል፡፡

ምክር ቤቱ አቶ ሱልጣን አልይን የድሬዳዋ  አስተዳደር ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ፣ ወይዘሮ  ጫልቱ ሁሴን ደግሞ የድሬዳዋ አስተዳደር ዋና ኦዲተር ጽህፈት ቤት ዋና ኦዲተር በማድረግ በሙሉ ድምጽ መርጧል፡፡

ከምክር ቤቱ አፈ-ጉባኤነት በተነሱት  አቶ አብዱሰላም መሐመድ ምትክ  ደግሞ አቶ ከድር ጁሃር ተመርጠዋል፡፡

ተሿሚዎቹ ህግና ሥርዓትን አክብረው የህዝቡን የልማት ፣ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ለመመለስና ሀገራዊ ለውጡን ከዳር ለማድረስ እንደሚተጉ ቃል ገብተዋል፡፡

ከአፈ-ጉባኤነታቸው የተነሱት አቶ አብዱልሰላም መሐመድ በራሳቸው ፍላጎት ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የኃላፊነት  ቦታውን መልቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

አዲሱ አፈ-ጉባኤ የተሳካ የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸውም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ኢብራሂም ዑስማን በምክር ቤቱ ጉባኤ ላይ እንደተናገሩት የህዝቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን መመመለስ ያቃታቸውና ሀገር አቀፉን ለውጥ  ማራመድ ያልቻሉ 76 አመራሮች ከሥልጣን እንዲነሱ ተደርጓል፡፡

27 አመራሮች  ደግሞ አቅማቸው በሚመጥናቸውና የተሻለ ውጤት ያስመዘግባሉ በሚባሉበት ቦታ በመመደብ የማሸጋሸግ ሥራ መከናወኑን ጠቁመዋል፡፡

ከቀበሌ ፣ከገጠር ክላስተርና ከካቢኔ ሥልጣናቸው በተነሱት ምትክ ብቃት ያላቸው ወጣት አመራሮች መተካታቸውን ነው ከንቲባው የገለፁት፡፡

አዲሶቹ አመራሮች ሀገር አቀፍና አስተዳደራዊ ለውጡን ለማሳካት  ግንባር ቀደም ሆነው መስራት እንደሚጠበቅባቸውም አመልክተዋል፡፡

60 በመቶ በሚሆኑ አመራሮች ላይ የተካሄደው ለውጥ ከ50 ሺህ በላይ ነዋሪዎች በተሳተፉባቸው መድረኮች የቀረቡትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግር  ለመፍታትም ወሳኝ   አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡

” አመራሩን የመፈተሸና የማጥራት ሥራ ቀጣይነት አለው፤ ተጠያቂነትን የማስፈን ሥራ ይጠናከራል ” ብለዋል ከንቲባው፡፡

የምክር ቤቱ አባል ወይዘሮ ኢፍቱ ዩሱፍ በበኩላቸው “ሥልጣንን በማሸጋሸግ ብቻ የህዝቡ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መንገድ ሊፈቱ አይችሉም” ብለዋል፡፡

ሥር-ነቀል እርምጃ በመውሰድ ሀገር አቀፉን ለውጥ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ሌላው የምክር ቤቱ አባል አቶ አብዲ ቡሌ በበኩላቸው የተወሰዱ እርምጃዎችን በወቅቱ ለህዝብ መግለፅ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

የምክር ቤቱን ውሳኔዎችና የአመራር ለውጡን በቅርበት እንደሚከታተሉ የተናገሩት የድሬዳዋ ነዋሪ አቶ ጃንቦ ታሪኩ  “አመራሩ ችግር ሲገጥም ብቻ ሣይሆን በየጊዜው ራሱን መገምገምና በህዝብም መተቸት አለበት ” ሲሉ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

አዲሱ ሹመትን አስመልክተው እንደገለፁት የትኛውም የሚሾም አካል ብቃትና ችሎታ ያለውና  ለውጡን ለማሳካት የሚተጋ መሆን አለበት፡፡

አቶ መሐመድ ዩሱፍ የተባሉ ነዋሪ  የጠበቁትን ያህል ባይሆንም የተወሰደው እርምጃ የሚበረታታና ሊጠናከር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡  (ምንጭ፡ ድሬዳዋ ማስ ሚድያ ኢንተርፕራይዝ))