የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

​​​​​​የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ይ በኢትዮጵያ ለሶስት ቀናት ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ ምሽት አዲስ አበባ ይገባሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት የሚያደርጉትን የመጀመሪያውን የውጭ ጉዟቸውን በኢትዮጵያ ይጀምራሉ ነው የተባለው።

በቻይና መንግስት አሰራር መሰረት ከፍተኛ ባለስልጣናቱ በየዓመቱ የሚያደርጉትን የመጀመሪያ የውጭ አገር ጉብኝት ቅድሚያ በሚሰጧቸው አገራት እንዲጀምሩ ይደረጋል።

ከቻይና መንግስት ጋር በትብብር በሚከናወኑ የግብርና፣ የኢንዱስትሪ፣ የመሠረተ ልማት፣ የአቅም ግንባታ እና የድህነት ቅነሳ ዘርፎች አፈፃፀም በቻይና መንግስት ኢትዮጵያ ከአፍሪካ እንደ ቀዳሚ አገር ትወሰዳለችም ተብሏል።

ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ በመገኘት ከከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር የሚያደርጉት ውይይት በሁለቱ አገሮች መካከል አሁን ያለውን የሁለትዮሽ እና የባለብዙ መድረኮች ሁሉን አቀፍ ትብብር ይበልጥ እንደሚያጠናክረው ይጠበቃል።

ሁለቱ አገሮች ከግንቦት ወር 2009 ዓም ጀምሮ ግንኙነታቸውን ወደ ሁሉን አቀፍ ስትራቴጂያዊ አጋርነት ትብብር ደረጃ ማሳደጋቸው የሚታወቅ ሲሆን ይህ ዓይነት ትብብር ቻይናም ሆነ ኢትዮጵያ ከጥቂት የዓለም አገራት ጋር ብቻ የመሠረቱት የትብብር ማዕቀፍ ነው።  

ሁሉን አቀፍ ትብብሩ ሁለቱ አገሮች በሁለትዮሽ፣ በባለብዙ ወገን፣ በህዝብ ለህዝብ፣ በንግዱ ማህበረሰብ እና በሌሎች መሰል የግንኙነት መድረኮች በትብብር ለመሥራት እንዲያስችላቸው ይፋ ያደረጉት የትብብር ዓይነት ነው።

ዋንግ ይ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እንዲሁም ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር ውይይት ያደርጋሉ።

ኢትዮጵያ እና ቻይና ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት በ1962 ዓም ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በበርካታ የሁለትዮሽእና የባለብዙ ወገን ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር በመሥራት ላይ ይገኛሉ፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)