መምህራን በትምህርት ቤቶችና በአከባቢያቸው ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቁ

መምህራን በትምህርት ቤቶችና በአከባቢያቸው ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡

የሰላም ሚኒስቴር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ሀገር አቀፍ መምህራን የሰላም ውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በዚህ የውይይት መድረክ ላይ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚልን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ  አካላት ተገኝተዋል፡፡

ውይይቱ “ሰላምና ሀገር ወዳድ መምህራኖች ፤ ሰላምና ሀገር ወዳድ ተማሪዎችን ያፈራሉ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን መምህራን በትምህርት ቤቶችና በአከባቢያቸው ሰላም እንዲረጋገጥ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ንግግር ያደረጉት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል መምህራን ትውልድን መቅረጽ ካላቸው እድል አንፃር ሰላምን በመስበክ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበርክቱ ይገባል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ግንባታ ትምህርትና የተሟላ ስብዕና የሚጠይቅ በመሆኑም ለማህበረሰብ ስብዕናና የበለጸገ ትውልድን በመፍጠር ረገድ የመምህራን ሚና ክፍተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ትምህርት ቤቶች የሰላም ማዕድ ይሆኑ ዘንድም መምህራን እያከናዎኑት ያለውን ትውልድን የመቅረጽ ተግባር አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸውም ወይዘሮ ሙፈሪያት አሳስበዋል፡፡     

በውይይቱ ላይ አስተያየት የሰጡት መምህራን በበኩላቸው ሰላም ሁሉንም የሚመለከት ጉዳይ በመሆኑ ሰላምን በመስበክና በማረጋገጥ ረገድ ከመንግስት ጋር በመሆን የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

በተለይም የስነ ዜጋ፣ ስነ ምግባርና የታሪክ ትምህርት መምህራን ለተማሪዎች በሚያቀርቡት ትምህርት ላይ ሚዛናዊና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ማቅረብ እንዳለባቸውም ጠቁመዋል፡፡  

መምህሩ በስነ ምግባር አርዓያ በመሆን ሰላምና ግብረ ግብነትን ሊሰብክ እንደሚገባም ተሳታፊዎቹ አንስተዋል፡፡

በውይይቱ ላይ መምህራን በሰላም ግንባታ ዙሪያ ሚናቸው ምን ሊሆን ይገባል የሚል የመነሻ ጽሁፍ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ይገኛል፡፡

ከሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የተወጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የሚሆኑ መምህራኖች በመድረኩ የተገኙ ሲሆን ውይይቱ እስከ ነገ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡