ምክር ቤቱ 110 የነበሩ የአስፈፃሚ ተቋማትን ወደ 63 ዝቅ አደረገ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 110 የነበረውን የአስፈፃሚ ተቋማት ቁጥር ወደ 63 ዝቅ አድርጓል፡፡

ምክር ቤቱ በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ኃብት ልማት ቢሮ ተረቀው የከተማውን አስፈፃሚ አካል እንደ አዲስ ለማዋቀር የቀረበውን አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

በአዲሱ አወቃቀሩም 38 ተቋማት በነበሩበት ሲቀጥሉ 14 ተቋማት በአዲስ ሁኔታ ተደራጅተዋል፡፡

በተጨማሪም 6 ተመሳሳይ ተልዕኮ የነበራቸው አስፈፃሚ አካላት የተዋሃዱ ሲሆን 5 ተቋማት እንደ አዲስ ተቋቁመዋል፡፡ 

በዚህም 110 የነበረው የአስፈፃሚ ተቋማት ቁጥር ወደ 63 ዝቅ እንዲሉ ተደርገዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ የማሻሻያ አዋጁ ያስፈለገበትን ዋነኛ ምክንያት ሲያቀርቡ የለውጥ ሂደቱን በትክክለኛ መንገድ ለማስኬድና የሪፎርሙ አካል መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 
እንዲሁም አዲሱ አወቃቀር ሪፎርሙን መሬት በማድረስ ረገድ የማይተካ ሚና ያለው ሲሆን ይህም አደረጃጀት ውጤታማነትን እና የተቋማት ተጠያቂነትን ያሰፍናል ብለዋል፡፡

በመጨረሻም ከንቲባ ታከለ ኡማ የአገልግሎት ሰጪው ሴክተር ስኬታማነት የሚለካው በህዝብ እርካታ መሆኑን እንዲሁም ተቋም እንጂ ስራ አይታጠፍም ሲሉም በአፅኖት ተናግረዋል፡፡

በምክር ቤቱ በፀደቀው አዋጅ መሰረትም የታጠፉት ተቋማት፦

1. የአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ
2.የመዋቅርና አደረጃጀት ፕሮጀክት ፅ/ቤት
3. ዴሊቨሪ ዩኒት
4. ካይዘን ኢንስትቲዩት
5. ወንዞችና ዳርቻዎች ልማትና የአየር ንብረት ለውጥ ማጣጣም ፕሮጀክት ፅ/ቤት
6. እንጦጦና አካባቢው ቱሪስት መዳረሻ ፕሮጀክት ፅ/ቤት
7.የመስሪያ ቦታዎች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ
8.ትራንስፓርት ፈንድ ፅ/ቤት
9.ትራንስፖርት ፕሮግራሞች ማስተባበሪያ ፅ/ቤት
10.ህብረተሰብ ተሳትፎ ልማት ኤጀንሲ
11.ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ
12. የተቀናጀ መሬት መረጃ ማዕከል
13.ማህበራዊ ጥበቃ ፈንድ እና ልማታዊ ሴተፍትኔት ኤጀንሲ
14.ደንብ ማስከበር አገልግሎት ፅ/ቤት
15.የውሃና ፍሳሽ ሳኒቴሽን ልማትና ማስፋፊ ፕሮጀክት ፅ/ቤት
16.የማዕከላትና ኮሪደር ልማት ኮርፖሬሽን
17. ሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር፣ ሽግሽግና ኢንኩቤሽን ማዕከል
18. ሬዚሊየንስ ፕሮጀክት ፅ/ቤት

በአዲስ መልክ የተቋቋሙ ተቋማት ደግሞ

1. ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ
2. የመንግስት ልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ባለስልጣን
3. የወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ
4. ግንባታ ኢንተርኘራይዝ
5. ግንባታ ዲዛይን ፅህፈት ቤት መሆናቸው ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-የከንቲባ ጽህፈት ቤት)