የመከላከያ ሰራዊቱን በኅብረተሰቡ ተወዳጅና በወጣቱ ዘንድ ተመራጭ የስራ ዘርፍ ማድረግ ይገባል – የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት

የመከላከያ ሠራዊት አባል መሆንን በኅብረተሰቡ ተወዳጅና በወጣቱ ዘንድ ተመራጭ የሥራ ዘርፍ ለማድረግ መሥራት እንደሚገባ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።

የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ሠራዊቱን በኅብረተሰቡና በወጣቱ ዘንድ ተወዳጅና ተመራጭ የስራ ዘርፍ  ለማድረግ እየተሰራ ካለው የለውጡ አንድ አካል መሆኑን ገልጿል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን 17ኛ መደበኛ ስብሰባው የመከላከያ ሚኒስቴርን የስድስት ወር የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ገምግሟል።

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በዚሁ ጊዜ ባነሱት ሐሳብ መከላከያ ሠራዊቱ ለህገ መንግስቱ የቆመና የሀገር ዳር ድንበርን አስከብሮ ሉዓላዊ አገር የማስረከብ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል።

በህገ መንግስቱ የተሠጠውን ተልዕኮ በብቃት በመወጣት በኅብረተሰቡ ዘንድ አመኔታን በመፍጠር ለወጣቱ ትውልድ ተመራጭ የሥራ ዘርፍ መሆን እንደሚገባውም አመላክተዋል።

የጦር ኃይሎች ምክትል ኢታማዦር ሹም ጄነራል ብርሃኑ ጁላ በሠጡት ገለጻም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የሚደረገው ለውጥ በወጣቶች ዘንድ ተመራጭ የስራ ዘርፍ እንዲሆን የሚያስችለው ነው ብለዋል።

“በአዲሱ አደረጃጀት በዩኒቨርሲቲ ደረጃ የተማሩ ወጣቶች ወደ ሰራዊቱ እንዲገቡ ይፈለጋል” ነው ያሉት ጄነራል ብርሃኑ።

ወጣቶች በጥቅም ተደልለው ወይም ተገደው ሳይሆን ወደ ውትድርናው መስክ  አፍቅረውት የሚገቡበት ተቋምና የስራ ዘርፍ ማድረግም እየተሰራ ያለው አደረጃጀት አካል መሆኑን ገልጸዋል።

መከላከያ ሰራዊቱን የኅብረተሰቡ የመጨረሻው ምሽግና መመኪያ ለማድረግም ኅብረተሰቡ የእኔ ነው የሚል ስሜት እንዲያጎለብት ማድረግም አንዱ ግባችን ነው ብለዋል።

የሠራዊቱን መሪዎችና አደረጃጀቱን በማብጠልጠል፣ ስም በማጥፋት፣ ውሸት በመፈብረክ ሰራዊቱ እንዲበተን በዚያውም ኢትዮጵያ እንድትፈርስ የሚታትሩ እንዲሁም የሰራዊቱን ክብር የሚነኩ አካላት ከድርጊታቸው መታቀብ እንዳለባቸውም አሳስበዋል ጄኔራሉ።

በመሆኑም መከላከያ ሰራዊቱን እንደ ጠላት የሚያዩ ቡድኖች ከወዲሁ አመለካከታውን ካልገሩ ጠንካራና በወጣቱ ዘንድ ተመራጭ ሰራዊት መገንባት አስቸጋሪ ስለሚሆን ነገሮችን ሰከን ብሎ በማሰብ አመለካከትን መቀየር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የመከላከያ ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሐመድ በበኩላቸው የተጀመረው ለውጥ ፍሬ አፍርቶ በወጣቶች ዘንድ ተመራጭ ሰራዊት ለመፍጠር  መገናኛ ብዙኃን ሊያግዙን ይገባል ብለዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባል መሆን የተከበረ፣ ሊኮሩበትና ሊተማመኑበት የሚገባ ዘርፍ መሆኑን በመገናኛ ብዙኃን በአግባቡ መተላለፍ ይገባልም ብለዋል።  ( ኢዜአ)