በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ 26 ክላሽ፣ አንድ ብሬንና 20 የጥይት ካዝና በቁጥጥር ስር ዋለ

በጋምቤላ ክልል በህገ ወጥ መንገድ ሲንቀሳቀስ የነበረ ሃያ ስድስት ክላሽ፣ አንድ ብሬንና ሃያ የጥይት ካዝና በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለፀ።

የጋምቤላ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን በኑዌር ብሄረሰብ ዞን ባደረገው ክትትል ሃያ ስድስት ክላሽ፣ አንድ ብሬንና ሃያ የጥይት ካዝና በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታውቋል፡፡

የጦር መሳሪያውን ሲያንቀሳቅስ የተገኘው ተጠርጣሪም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ሳይመን ቲያች ተናግረዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በጉዳዩ ዙሪያ ፖሊስ ምርመራ እያካሄደ ሲሆን ፥የምርመራ ሂደቱ እንደተጠናቀቀም  ውጤቱ ለፍርድ ቤት የሚላክ መሆኑ ነው የተገለፀው።

ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎቹና ተጠርጣሪ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የዋሉትም  በህብረተሰቡ ጥቆማና ፖሊስ ባደረገው የተጠናከረ የክትትልና የቁጥጥር ስራ መሆኑን ከጋምቤላ የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

የፀጥታ አካላት የህገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት ህብረተሰቡ የተለመደ ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚሽነሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የጋምቤላ ክልል ከደቡብ ሱዳን ጋር ከሚጋራው ሰፊ የድንበር ወሰን ጋር ተያይዞ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ወደ ክልሉ እየገባ መሆኑም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ (ምንጭ ፡  ኤፍ.ቢ.ሲ)