በማረሚያ ቤቶች ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ መሻሻሉን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር አስታወቀ

ባለፉት ስድስት ወራት በማረሚያ ቤቶች ያለው የሰብአዊ መብት አያያዝ መሻሻሉን የፌደራል ማረሚያ ቤቶች  አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ  ጀማል አባሶ ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ በተቋሙ ያለውን አጠቃላይ አሠራር ለማሻሻል የተለያዩ ሪፎርሞች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በሃገሪቱ ባለፉት ዓመታት በማረሚያ ቤቶች ሰፊ የሆነ የሰብአዊ መብት ጥሰት ይፈጸም እንደነበር የተለያዩ ከማረሚያ ቤት የወጡ እማኞች ምስክርነታቸውን መሥጠታቸው ይታወሳል ።

በአስተዳደሩ  ሥር በሚገኙ  ስድስት ማረሚያ ቤቶች በተደረገ ያሰሳ ጥናት ከዚህ ቀደም የነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰት መሻሻሉን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ከዚህ የበለጠ መሥራት እንደሚያስፈልግና ለዚህም ተጨማሪ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አስረድተዋል ።

በሌላ በኩል የአስተዳደሩን የፍትህ ሥርአት ለማሻሻልም ከላይ እስከ ታች ያሉትን 103 አመራሮች ላይ የመተካካት ሥራ መሥራቱን ዋና ዳይሬክተሩ ገልፀዋል።

የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ተልዕኮ ይበልጥ ለመፈጸምና የነበሩ ክፍተቶችን ለማስተካከልም ተቋማዊ ሪፎርም ስትራቴጂክ ዶክመንት በማዘጋጀት የተቋማዊ መዋቅር ማሻሻያ ተግባራዊ በማድረግ ለታራሚዎችና ለተቋሙ 700 ሠራተኞችም የተለያዩ ሥልጠናዎች እየተሠጠ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ባለፉት ስድስት ወራት በመደበኛ ይቅርታ በአመክሮ በምህረትና በተለያዩ የፍርድ ቤት ውሳኔዎች 6ሽህ 504 የሚሆኑ ታራሚዎች መለቀቃቸውን አስታውቀዋል፡፡