በኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ዳግም መጀመር የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ሊመሰገኑ ይገባል—ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል

የኢትዮጰያ እና የኤርትራ ህዝቦች ግንኙነት ዳግም እንዲጀመር ላደረጉ ለሁለቱ ሀገራት መሪዎች ምስጋና እንደሚገባቸው የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ገለጹ።

የተጀመረውን የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት ለማጠናከር በማሰብ የሁለቱ ሃገራት አጎራባች ህዝቦች በሰቲት ሁመራ ተከዜ ወንዝ ድንበር ላይ አክብረዋል።

በስነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ-መስተዳደር ዶክተር ደብረጽዮን እንደተናገሩት የተቋረጠውን የሁለቱ ሃገራት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት እንዲጀመር ያደረጉት አቶ ኢሳያስ አፈወርቂና ዶክተር አብይ አህመድ ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል።

በኢትዮጰያ የትግራይ ምዕራባዊ ዞንና በኤርትራ ጋሽ ባርካ አጉራባች ህዝቦች ከእንግዲህ የተጀመረውን የሰላም ግንኙነት በማጠናክር ቀጣይ ጉዟቸውን ብሩህ ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ለግንኙነቱ ዘላቂነትም የትግራይ ክልላዊ አስፈላጊውን ተግባራት ሁሉ እንደሚያከናውንም አስረድተዋል።

የትግራይ ምዕራባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ርስቁ አለማው በበኩላቸው “የተጀመረ ሰላም ዘላቂ  እንዲሆን  እንሰራለን” ብለዋል።

የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱና የአካባቢው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ነዋሪዎቹ በጋራ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የጋሽ ባርካ ተወካይና የጉልጅ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሓጎስ ዓምደ ብርሃን ”የተጀመረው ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እንሠራለን ከእንግዲህ ይህን ሰላም እንጠብቀዋለን ማንም አያቋርጠውም” ብለዋል።

የሰቲት ሁመራ ነዋሪ አቶ ይመሰል ከዋኒ እንዳሉት በአካባቢያቸው ዘላቂ ሰላም ተረጋግጦ ከወገኖቻቸው ጋር መገናኘት መቻላቸው አስደስቷቸዋል።

“የተጀመረ ሰላም እንዳይቋረጥ ሁለቱም መንግስታት በቅን ልቦና ሊሰሩ ይግባል እኛም የተጀመረውን ሰላም አጠናክርን እንቀጥልበታለን”በማለት ተናግረዋል።

የኦምነ ሓጀር ነዋሪ መሓመድ ብርሃን ዑስማን በበኩላቸው ከ21 አመት በኋላ እንደዚህ ብለን መገናኛታችን ደስ ብሎናል ሰላሙ ቀጣይ እንዲሆንም እንሰራለን ብለዋል።

በተከዜ ወንዝ ዳርቻ በተካሄደው ስነ-ስርዓት ላይ ዶክተር ደብረጽዮንን ጨምሮ የክብር አቀባበል የተደረገላቸው የጋሽ ባርካ ነዋሪዎችና ተወካዮች፣ የሃይማኖት አባቶች እና የምዕራባዊ ትግራይ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። (ኢዜአ)