ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ በ147 ጠበቆች ላይ እርምጃ ወሰደ

ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ከስነ ምግባር ጋር በተያያዘ በ147 ጠበቆች ላይ እርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የጠበቆች አስተዳደር ና የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ደምሴ እንደገለጹት፥ የስራ ክፍሉ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ውስጥ ውሳኔ ካገኙት 175 መዝገቦች ውስጥ 147 ጠበቆች ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡

ከ175 መዝገቦች ውስጥ 5 በስነ ምግባር ችግር ጥፋተኛ ተብለው የታገዱ፣ 77 ፈቃድ በወቅቱ ባለማደስ በገንዝብ የተቀጡ፣ 54 ፈቃድ ባለማሳደስ ለጊዜው የታገዱ፣ 7 በስነ ምግባር ችግር ጥፋተኛ ተብለው በገንዘብ የተቀጡ ሲሆን አራቱ ደግሞ በማስጠንቀቂያ በነፃ ተሰናብተዋል፡፡

በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የጠበቆች አስተዳደር ና የነፃ የህግ ድጋፍ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ለፌደራል ማናቸውም ፍርድ ቤቶችና መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መቆም ለሚችሉ አዳዲስ ጠበቆች የሙያ ብቃትና ስነ-ምግባር ሲያሟሉ በፈተና እና ያለ ፈተና የጥብቅና ፈቃድ እንደሚሰጥም አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡

የሙያ ግዴታቸውን በአግባቡ ለተወጡ ጠበቆች በየዓመቱ የጥብቅና ፈቃድ ማደስ፣ ጠበቆች የገንዘብ አቅም ለሌላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ነፃ የህግ ምክርና የጥብቅና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ፣ ምትክ የጥብቅና ፈቃድ መታወቂያ ደብተር መስጠትም ዳይሬክቶሬቱ የሚያከናውናቸው ተግባራት ናቸው።

(ምንጭ፡-የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ )