የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለሚደረገው ውይይትና ድርድር 32 አጀንዳዎች ቀረቡ

የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ለሚደረገው ውይይትና ድርድር 32 የተለያዩ አጀንዳዎችን  አቅርበዋል ።   

ፓርቲዎቹ በቀጣይ በሚያደርጉት ውይይት እና ድርድር ዙሪያ ከምርጫ ቦርድ ጋር ለሁለት ቀን መክረዋል።

ትናንት በተካሄደው የማጠቃላያ ውይይት ላይ ፓርቲዎቹ የውይይት አጀንዳ ቢሆኑ ብለው ለብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከ32 አጀንዳዎችን በፅሁፍ አቅርበዋል ።

ፓርቲዎቹ ካነሱት አጀንዳዎች መካከል ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ፣የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት፣ትብብር እና ጥምረት፣የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት፣ የምርጫ መራዘም፣የ2012 ምርጫ፣ ሰላም እና መረጋጋት፣ የፀጥታ እና ደህንነት ተቋማት ግንባታ እና ማሻሻያ፣ የህገመንግስት ማሻሻያ፣የስራ ቋንቋ፣ የአዲስ አበባ ጉዳይ፣ ሰንደቅ ዓላማ፣የመንግስት አደረጃጀት እና የክልሎች አደረጃጀት የሚመለከቱ ጉዳዮች ይገኙበታል።

በምክክር መድረኩ  የፖለቲካ ፓርቲዎች እና ድርጅቶች በቀጣይ የውይይት እና ድርድር ደንብ ላይ እየመከሩ ሲሆን፥ 16 አንቀፅ ያለው ረቂቅ ደንብ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ ላይ የቀረበው የውይይት ደንብ የውይይት አላማ፣ መርህ፣ የአወያይ አመራረጥ እና ሚና እንዲሁም የታዛቢዎች አመራረጥን ያካተተ ነው።

በረቂቅ የደንቡ መሠረት ውይይቱ በገለልተኛ አወያዮች የሚመራ ሲሆን፥ አወያዮቹም ገለልተኛ እና በፓርቲዎቹ ይሁንታ የሚመረጡ እንደሚሆኑ ተገልጿል።

ታዛቢን በሚመለከት የሙያ፣ የሰራ እና የንግድ ማህበራት በታዛቢነት እንዲሳተፉ በረቂቁ ተደንግጓል።

የረቂቅ ደንቡ ውሳኔ አሠጣጥን ቢቻል ፓርቲዎች በስምምነት በውሳኔ እንዲያሳልፉ፤ ይህ ባይሆን አወያዩ የስምምነት ሃሳብ እንዲያቀርብ፣ ስምምነት ካልመጣም  የማስማሚያ ሀሳብ ያቀርባል ይላል የረቂቅ ደንቡ።

በዚህ መንገድ ፓርቲዎቹ በተወያዩበት ሀሳብ በእለቱ መስማማት ካልቻሉ ጉዳዩ በአብላጫ ድምፅ እንደሚወስንም በረቂቁ ተደንግጓል።

ፓርቲዎችም ረቂቅ ደንቡ ለታዛቢ የማይገባውን ሥልጣን ሰጥቷል፤ የአብላጫ ድምፅ ውሳኔ አያስኬድም የሚሉ እና ሌሎች ጥያቄዎችን አቅርበዋል።

የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ስብሳቢ ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳ ለጥያቄዎቹ በሠጡት ምላሽ ታዛቢ በፈለገው ሰዓት ጣልቃ የመግባት ስልጣን ነማለት የአብላጫ የድምፅ ውሳኔን በተመለከተ ሌላ የውሳኔው ስልት ማምጣት እንደሚችሉ ጠቁመዋል ።