የመከላከያ መማክርት ዛሬ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አደረገ

የመከላከያ መማክርት በዛሬው ዕለት በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ውይይት አድርገዋል፡፡

በውይይቱ ላይ መከላከያ ሠራዊት በህጋዊ ማዕቀፎች፣ በአደረጃጀት፣ በመፈጸም ብቃትና በትጥቅ በከፍተኛ የለውጥ ጎዳና ላይ እንደሚገኝ ተነስተዋል፡፡

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የመሩት ይህ ውይይት የሰራዊቱን ለውጥ በሁሉም ደረጃ ተፈፃሚ ከማድረግና ወደ ታች ከማውረድ አንጻር የተገኙ ተጨባጭ ውጤቶች፣ የታዩ ክፍተቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ዙሪያ ውይይት እንደተደረገባቸው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

መማክርቱ መከላከያ እስካሁን ያደረጋቸው የተቋማዊ ማሻሻያ ስራዎች ምን ያህል ርቀት እንደተጓዙ በመገምገም በቀጣይ ትኩረት ሊሰጣቸዉ በሚገባ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ አቅጣጫ ማስቀመጡም ተመልክቷል።

የሀገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠንም ቴክኖሎጂን የሚታጠቅ፣ በራሱ አቅም መጠገን፣ ማሳደግ ብሎም መፍጠር የሚችል እንዲሆን በርካታ የአቅም ግንባታ ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑም ነው የተነሳው።

መከላከያ ከቴክኖሎጂ ጋር ጥብቅ ቁርኝት ያለውና እንደሌሎች ሃገራት ከራሱ አልፎ ለሌሎች የቴክኖሎጂ ዘርፎች ምንጭ መሆን የሚችል የቴክኖሎጂ ማዕከል እንዲሆን እየተሰሩ ያሉ ሥራዎችም ተገምግመዋል።

በሁሉም ደረጃዎች የሁሉንም ብሔር ብሔረሰቦች ተዋጽኦ የጠበቀ ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራትም በውይይቱ ታይተዋል።

ከዚህም ባሻገር የሀገሪቱን ወቅታዊ ውስጣዊና ከባቢያዊ ሁኔታን ታሳቢ ያደረገ የሠራዊት አሰፋፈር እንዲኖር የተጀመረመው እንቅስቃሴ ላይ ሰፊ ውይይት የተደረገ ሲሆን፥ በዚህም የመከላከያ ሠራዊት አሰፋፈር ወቅታዊ፣ ተጨባጭና ታሳቢ ስጋትን መሰረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን በመሆኑ ሕብረተሰቡም በዚህ መልኩ እንዲረዳው ማድረግ አስፈላጊ መሆኑም ተነስቷል።

የሠራዊት እንቅስቃሴው እንደ አዲስ ከማስፈርም ባሻገር ለረጅም ጊዜ በድንበር ምሽግ ውስጥ የነበሩ የመከላከያ አባላትን ወደ ሥልጠናና አቅም ግንባታ ሥራዎች ማስገባት የአጠቃላይ ተቋማዊ ማሻሻያ አካል በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ሁሉም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግ ጥሪ ተላልፏል።

በሁሉም ረገድ መልካም የአፈጻጸም ጅምሮች እንዳሉ የገመገመው መማክርቱ፥ በቀጣይ እነዚህን ለውጦች አጠናክሮ ለመቀጠል የሚስችሉ ሥራዎች እንዲሰሩ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡ (ምንጭ፡-የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት)