ኢንጂነር አይሻ መሀመድ ከጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኡመር ጌሊ ጋር ተወያዩ

የኢፌዲሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ የሚመራ ልዑካን ቡድን ከጅቡቲ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጌሊ ጋር ተወያዩ፡፡

በትላንትናው ዕለት በጅቡቲ ባደረጉት ውይይት ፕሬዝዳንት ኡመር ጊሌ የሁለቱ ህዝቦች ዘመን የማይሽረው ወዳጅነት የበለጠ እየተጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢንጂነር አይሻ ከዶክተር አብይ አህመድ የተላከ መልዕክት ለፕሬዝዳንቱ ያቀረቡ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት የህዝቦቻቸውን ጥቅምና ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ገልጸው ሁለቱ ወገኖች የተስማሙባቸው የልማት ውጥኖች ተግባራዊ እንዲሆኑ በጋራ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡

የጅቡቲው ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኡመር ጌሊ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት ለአፍሪካ ቀንድና ለአህጉሪቱ ተምሳሌት መሆኑን ለልዑካን ቡድኑ አስረድተው ይኸው ወንድማዊ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል መንግስታቸው እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የልኡካን ቡድኑ ከሁለትዮሽ ግንኙነቱ መጠናከር ጎን ለጎን በአካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ውይይት ማድረጋቸውም ተገልጿል፡፡ (ምንጭ፡-የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ ጽህፈት ቤት)