በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት- ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

በኢትዮጵያ የተገኘውን ለውጥ መጠበቅና ማስቀጠል የእያንዳንዱ ዜጋ ኃላፊነት መሆን አለበት ሲሉ የአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተናገሩ።

ንቅናቄው “ኢትዮጽያዊነትን እናወድስ” በሚል መሪ ቃል ያዘጋጀው የሙዚቃ ኮንሰርት በትናንትናው እለት በአዲስ አበባ ሚሊኒየም አዳራሽ ተካሂዷል።

በኮንሰርቱ ላይ መልእክት ያስተላለፉት ፕሮፌሰር ብርሃኑ፥ በኢትዮጵያ አሁን ያለውን አንድነት ለማጠናከር የቀደመውን አንድነት ማሰብ ያስፈልጋል ብለዋል።

“የሙዚቃ ኮንሰርቱም አንድነታችንና ኢትዮጵያዊነታችንን እያሞገስን በሀገሪቷ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የበኩላችን ለመወጣት ቃላችንን ዳግም የምናድስበት ነው” ብለዋል።

ኮንሰርቱ ኢትዮጵያዊነትን ከማወደስ ባሻገርም ንቅናቄውን በመላው ሀገሪቱ ለማደራጀት የሚያስችል ገቢን ለማሰባሰብ ያለመ ነው።

በሙዚቃ ኮንሰርቱ ላይም የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ ተዋካዮች የተገኙ ሲሆን፥ታዋቂ የሙዚቃ ባንዶች፣ ወጣትና አንጋፋ ድምጻውያን ተሳትፈዋል።(ኤፍቢሲ)